ፈረስ – እንጅባራ በጊዮርጊስ፤ አጅባር በመርቆሪዮስ!

559
ፈረስ – እንጅባራ በጊዮርጊስ፤ አጅባር በመርቆሪዮስ!
ባሕር ዳር፡ ጥር 25/2013 ዓ.ም (አብመድ) ጥር የወራት ሁሉ ሙሽራ ነው፤ በሀገራችን በጫጉላ ውስጥ የሚያልፍ ብቸኛው ወር ጥር ብቻ ነው፡፡ በተለይ በአማራ ክልል ጥር ከዋዜማው እስከ ድራሩ በድምቀት እንደተከበረ ያልፋል፡፡ ጥር በማኅበራዊ ትስስሩ፣ በሐይማኖታዊ ቀኖናው፣ ቱሪዝምን መሰረት ባደረገው ምጣኔ ሃብታዊ ጥቅሙ እና ጥንታዊ ቀደምትነትን በሚያጎላው ባህላዊ እሴቱ ፋይዳው የጎላ ነው፡፡
ጥር በአማራ ክልል ሕዝቦች ዘንድ በተዝናኖት ያልፋል ቢባል አልተጋነነም፡፡ የመነን ቀሚስ የቻይና ሱሪን ያስንቃል፡፡ እንሶስላ በጥፍር ቀለም ተተክቶ ይደምቃል፡፡ ኩል፣ አደስ እና አርቲ ቻፕስቲክን፣ ሊፕስቲክን እና ሽቶን ያስንቃሉ፡፡ ቁንጮ፣ ጋሜ እና ሹርባ ቅጥ ያጣውን ዘመናዊ የፀጉር አሰራር ተክተው ይውላሉ፡፡ ድሪ፣ አምባር፣ አልቦና ጥርስም የውበት ዳርቻ፣ የልጃገረዶች ያጊያጊያጥ ቀንዲል ይሆናሉ፡፡ ሎሚ በተረከዘ ሎሚ ደረት ላይ ሁሉ ይወረወራል፡፡
ለጥንታዊው የእጭት ስርዓትም ጥር መሰረት ነው፡፡ ጥር በኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት መዓዛ ተጀምሮ ይጠናቀቃል፡፡ የጥንታዊ ጀግንነት ባቡር የነበረው ፈረስ በአማራ ክልል ሕዝቦች የወርሃ ጥር በዓል ትርዒትን አድምቆ ያልፋል፡፡ በተለየ ሁኔታ ፈረስ እንደሰው ልጅ የሚታዘዝላቸው ሕዝቦች ደግሞ አሉ፡፡ እንጅባራ በጊዮርጊስ፣ አጅባር በመርቆሪዎስ የፈረስ ትርዒትን እንደ እንዝርት ያሾሩታል፡፡
ፈረስን እንደ አክሱም ሃውልት ቀጥ አድርገው የሚያቆሙት አገዎች በእለተ ጊዮርጊስ ቀልብ ይማርካሉ፡፡ ሽምጥ ጋልበው ተጋጣሚዎቻቸው ላይ ልምጭ እንደቀስት የሚተክሉት የራስ ጉግሳ ወሌ ልጆች በአጅባር ሜዳ ላይ እንደሚግ ሲወረወሩ ላየ ትንግርት ይሆንበታል፡፡
ተቀራራቢ መልካ ምድራዊ አቀማመጥ እና የአየር ፀባይ ያላቸው የአገው ምድሯ መዲና እንጅባራ እና የበጌምድሯ መናገሻ ደብረ ታቦር የፈረስ ግልቢያ ጌጥም ያመሳስላቸዋል፡፡ ጥንታዊ ኢትዮጵያዊያን ሃገርን ከወራሪ ለመታደግ ገስግሰው የሚደርሱበት ፈረስ እንደነገስታቱ ሁሉ ስያሜ ነበራቸው፡፡ ከአባ ታጠቅ እስከ አባ በዝብዝ፤ ከአባ ዳኘው እስከ አባ ጠቅል፤ ከአባ ግርሻ እስከ አባ ባሕር፤ ከአባ መቻል እስከ አባ ውቃው ነገስታቱ እና መኳንንቱ ለፈረሶቻቸው የሚሰጧቸው ስያሜዎች ነበሩ፡፡
ጥንታዊ ባህልን እና እሴትን በሚያጎላው የወርሃ ጥር የዓደባባይ በዓላት ላይ ፈረስ በአማራ ክልል ሕዝቦች ዘንድ ድምቀት ሆኖ ያልፋል፡፡ ይህንን ውብ እና ነባር እሴት አጉልቶ ለቀሪው ዓለም ለማስተዋወቅ ግን በበቂ ተሰርቷል ለማለት ይከብዳል፡፡ ጥንታዊ ማንነትን ጮክ አድርገው በሚናገሩ እሴቶቻችን ላይ መሥራት ፋይዳው ዘርፈ ብዙ ነው፡፡
በታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleቁንዝላ የተቀናጀ ፕሮጀክት በሳንክራ ገነታ ቀበሌ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራውን በይፋ ጀመረ።
Next articleየሴቶችን ውሳኔ ሰጭነት እና አመራርነት ሚና ማሳደግ የሁሉም ድርሻ መሆኑን ሴት የሥራ ኀላፊዎች ገልጹ፡፡