
ቁንዝላ የተቀናጀ ፕሮጀክት በሳንክራ ገነታ ቀበሌ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራውን በይፋ ጀመረ።
ባሕር ዳር፡ ጥር 25/2013 ዓ.ም (አብመድ) ቁንዝላ የተቀናጀ ዘላቂ የልማት ፕሮጀክት የጣና ዳርቻ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ነው። ፕሮጀክቱ በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰሜን አቸፈር ወረዳ በስድስት ቀበሌዎች በተፈጥሮ ሃብት ሥራ፣ በንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ በአካባቢ እና ግል ንፅህና ሥራን ይሠራል፡፡ ጥር 24/2013 ዓ.ም በሳንክራ ገነታ ቀበሌ የክልል እና የፌዴራል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት የተፈጥሮ ሃብት ሥራውን በይፋ ጀምሯል። ፕሮጀክቱ የኅብረተሰቡን ኑሮ ለመቀየር በጥናት ላይ ተመስርቶ ሥራ መጀመሩን የፕሮጀክቱ ዋና ዳይሬክተር ጌቴ ዘለቀ (ዶክተር) ተናግረዋል።
ወደ ጣና ሐይቅ የሚገባ ደለል የሐይቁን ህልውና እየጎዳው በመሆኑ የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ሥራን በአግባቡ በመስራት ሐይቁን መታደግ እንደሚገባም ዶክተር ጌቴ አሳስበዋል።
በዚህ ዓመት በሰሜን አቸፈር ወረዳ በ27 ቀበሌዎች 724 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ እና በ42 ተፋሰሶች ላይ የማሳ ላይ እርከን፣ የቦርቦር ማዳን ሥራ፣ የማፋሰሻ ቦዮች እና የተራቆቱ መሬቶችን ከልሎ የማልማት ሥራ እንደሚሰራ ከወረዳ አስተዳደሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ፋንታ ማንደፍሮ (ዶክተር) “የኅብረተሰቡን ህይወት ለመቀየር ብዙ ጊዜ ከማውራት ወጥተን ሥራ መስራት ላይ ማተኮር ይገባናል” ብለዋል። መሬቱ በእንክብካቤ ባለመያዙ ምርትና ምርታማነትቱ ቀንሶ ኅብረተሰቡን ለችግር እየዳረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ኅብረተሰቡ በአካባቢው የእኔነት ስሜት ተሰምቶት የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባውም ዶክተር ፋንታ መልእክት አስተላልፈዋል።
ፕሮጀክቶች የአካባቢውን ኅብረተሰብ ለመደገፍ አስተዋፅኦ እንዳላቸው የተናገሩት ምክትል ርዕስ መስተዳደሩ ኅብረተሰቡን በቀጥታ አሳታፊ አለማድረግ እና ኅብረተሰቡም በባለቤትነት አለመያዙ ሥራው ውጤታማ እንዳይሆን ያደርግ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ ፕሮጀክቶች ውጤታማ እንዲሆኑ ኅብረተሰቡ መደገፍ እንዳለበትም አሳስበዋል። የክልሉ መንግሥትም ለፕሮጀክቱ ውጤታማነት የቅርብ ክትትል እንደሚያደርግም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
በተፋሰሶች ላይ ቋሚ አትክልቶችን በማልማት፣ እንስሳትን አስረው በመቀለብ ተጠቃሚ መሆናቸውንም ነው ያነጋገርናቸው የአካባቢው አርሶ አደሮች የገለፁት። የቁንዝላ የተቀናጀ የመሬት አያያዝ፣ የንፁህ መጠጥ ውኃ፣ የአካባቢና የግል ንፅህና ፕሮጀክትን በመደገፍ የአፈርን ለምነት በመጠበቅ፣ የተሻለ ምርት በማምረት ተጠቃሚ ለመሆን እንደሚሰሩም ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ ሥራውን ባስጀመረበት ሳንክራ ገነታ ቀበሌ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ክብርት ወርቅ ሰሙ ማሞ፣ የእንጅባራ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ብርሃኑ በላይ፣ የኢፌዴሪ ውኃና መስኖ ኢነርጅ ሚኒስትር ዲኤታ አብርሃም አዱኛ (ዶክተር) እና ሌሎች የዞን፣ የክልል እና የፌደራል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፦ አማረ ሊቁ – ከምዕራብ ጎጃም ዞን
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ