
አጅባር ተጨነቀች፣ ቀደምቷ ከተማ በደስታ ዘለለች!
ባሕር ዳር ፡ ጥር 25/2013 ዓ.ም (አብመድ) ሩቅ በሚያስበው ንጉሥ ሩቅ የታሰበባት፣ ዘመናዊነት የተጀመረባት፣ ጀግኖች የተወለዱባት፣ ሃይማኖት የታነፀባት፣ ታንፆም የፀናባት፣ መለኮት በተገለጠበት ቅዱስ ሥፍራ ሥም የወረሰች፣ ሌሎች ሳይዘምኑ ዘመናዊነትን የጀመረች፣ ሌሎች ሲዘምኑ የተረሳች ቀደምት።
ያቺ የስልጣኔ ማዕበል ሊያጥለቀልቃት፣ ዘመናዊነት ሊያስጨንቃት የነበረች ባለተስፋዋ ከተማ ከአድማስ ባሻገር ያለውን የማለዳ ጀንበር ገልጦ ሊያሳያት የነበረው ታላቁ መሪ ጠፋባት። አብዝታ አዘነች፣ የነጋጋው ሌሊት ዳግም መሸባት፣ ግርማዋን ተነጠቀች፣ ሞገሷን አጣች።
ንጉሧን ብታጣም ታዲያ እምነቷን አላጎደለችም፣ ከጀግንነቷ አልቀነሰችም፣ ሩቅ አሳቢውን ንጉሥ ብታጣውም ሩቅ ያሰበው ህልሙ ይሳካ ዘንድ የሀገር ደጀን ሆና ፀናች የቴዎድሮስ ከተማ ደብረታቦር።
ሴባስቶፓል የተሰራባት፣ ኢትዮጵያዊነት የፀናባት፣ የቴዎድሮስ ራዕይ የታየባት፣ ዘመናዊነት ሀገር ንድፍ የተነደፈባት ናት።
“ወተትና ማሩ መጠጡ እያለለት፣
አንበሳው ቴዎድሮስ ለጠማው ጉሮሮ ባሩድ ጨመረበት”
እንደተባለ ራዕይ የተጠማው መሪ፣ አንድነት ተጠምታ የቆየችውን ሀገሩ ኢትዮጵያን አንድ አደረገ። ዘመናዊነት ሊያሳያት ከአድማስ ሊያሻግራት የማይተኛላት ኢትዮጵያን ከፍ ሊያደርግ እንደኳተነ መቅደላ ላይ ባሩድ ተጎንጭቶ አለፈ። ያለፈው ግን ስጋው ነው። መንፈሱና ራዕዩ ዛሬም አላለፈም፣ ነገም አያልፍም፣ አይጠፋም።
ባለ ብዙ ታሪኳ ደብረታቦር በአፄ ሰይፈ አርእድ ዘመነ መንግሥት እንደተመሰረተች ይነገርላታል። የመመስረቻ ዘመኗም ከ1327 እስከ 1361 ዓመተ ምሕረት ባለው ነው። ጥንተ አመሰራረቷም በኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን የቅዳሴ መሬት ላይ ነበር ይባላል።
ለረጅም ዘመናትም የባላባቶች መቀመጫ ሆና ዘለቀች። መልካሙ አየሯ ለመልካሙ ሕዝብ ምቹ ነበረችና እየተወደደች መጣች። ዘመን ዘመንን እየተካ ሲሄድ ከተማዋም እየሰፋች ሄደች። ንጉሡ ቴወድሮስ መቀመጫው ካደረጋት በኋላ ዘመናዊነትን ጀመረች። በራስ ጉግሳ ወሌ የግዛት ዘመን ከተማዋ እየሰፋችና ነዋሪዎቿ እየተበራከቱ ሄዱ።
ይህች ኢየሱስ ክርስቶስ ግርማ መለኮቱን በገለጠበት ተራራ ሥም የተሰየመችው ደብረታቦር ከከተማዋ አስቀድሞ የኢየሱስ ቤተክርስቲያን የሚገኝበት ሥፍራ ደብረ ታቦር የሚለውን ሥያሜ እንዳገኘ ይነገራል። ይሄውን ውብ ሥያሜም ከዚሁ ሥፍራ ወሰደች። በዚያውም ፀናች። ጥንታዊቷ ከተማ የባህል፣ የሃይማኖትና የታሪክ መገኛ ናት። ቀዳሚው የጋፋት ኢንዱስትሪ መንደር የተገነባባት ቀዳሚት ናት ደብረታቦር። የነገሥታት ስጦታዎች፣ ቅርሶች፣ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ የመስህብ ቦታዎች መገኛም ናት።
ደብረታቦር ስትነሳ አብያተክርስቲያኖቿ ይነሳሉ። አብያተክርስትያናቱ ሲነሱም ከተማዋ ትነሳለች። መሠረቷን የጣለችበት ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ተቀዳሚው ነው። ይህ በጥበብ ተሠርቶ በጥበብ የኖረ ቤተመቅደስ በኢትዮጵያ ብቸኛው የተክሌ አቋቋም ዝማሜ ማስመስከሪያ ዩኒቨርስቲ መገናኛ ነው።
የነገሥታት የስጦታ እቃዎች ቅርሶችም ይገኙበታል። ሰመርነሃ የተሰኘው የአፄ ዩሐንስ አራተኛ ቤተ መንግሥትም በዚህቺው ከተማ ይገኛል። አፄ ዩሐንስ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሆነው አገራቸውን እየተዘዋወሩ ሲመለከቱ ደብረ ታቦር አሁን ሰመርነሃ ከተባለው ቦታ ደረሱ። ቦታውንም ስለ ወደዱት ስሙን ሰመርነሃ ሲሉ ሰየሙት። ቃሉ የግእዝ ነው። ትርጓሜዉም ወደድናት ማለት ነው ይባላል። የተወደደችውን ከተማ እንድትወደድ የሚያደርጋት ብዙ ነገር አላት።
በወረሃ ጥር ደብረታቦር ታቦታቱን እያነገሠች እርሷም ትነግሳለች። ወረሃ ጥር የደብረታቦር መሞሸሪያ ነው። ውብ ኢትዮጵያዊት ሙሽራ። ያልጎደፈች፣ ያላደፈች፣ መልካም ሙሽራ።
የእግዚአብሔር መላዕክ የሚመራቸው ሁለት ወንድማማቾች ነበሩ። አምላካቸውን በልባቸው ይጠብቁታል። አብዝተው ያመሰግኑታል። እየፈሩ ይገዙለታል። እርሱም አብዝቶ ይወዳቸዋል። ይጠብቃቸዋል። ለእነዚህ ቅዱሳን ወንድማማቾች የእግዚአብሔር መላዕክ ሁለት ፅላት ሰጣቸው። ፅላተ ፅዮንና ፅላተ ማርያምን። በመንገዳቸው ሁሉ ይጠብቃቸውና ይመራቸው ነበር። በእርሱም እየተመሩ በደብረታቦር ደረሱ። በዚያውም በአንደኛው ሥፍራ ቤተመቅደስ አንፀው አንደኛውን ፅላት እንዲያሳርፉ አዘዛቸው። ቤተ መቅደስም ሠሩ። ታቦተ ማርያምን አስገቡ። አንድ ዓመት ከአራት ወራትም ቆዩ። ሌላ ቤተመቅደስ እንዲሰሩ ታዘዙ። ሠሩም። ታቦተ ፅዮንን አሳረፉ። ስያሜያቸውንም አስቀድማ ያረፈችውን መንበረ ብርሃን እናቲቱ ማርያም። ተከትላ ያረፈችውን መንበረ ንግሥት ልጅቱ ማርያም አሏቸው።
ልጅቱና እናቲቱ ማርያም የሚባሉ ታቦታት የሉም። ታዲያ ስያሜው ከዬት መጣ ካሉ ግን አመሠራረታቸው ፊትና ኋላ ስለነበር የቀደመችውን እናቲቱ የዘገየችውን ደግሞ ልጅቱ አሏቸው። ስያሜያቸውንም ይህንኑ ለማመላከት ነው። በዚሁ ስያሜም ዘለቁ።
ሌላ ዘመን መጣ። በመንበረ ንግሥት ልጅቱ ማርያም ቤተመቅደስ ውስጥ ተጨማሪ ፅላት ገባ። ይሄም ታቦተ መርቆሬዎስ ነው። መርቆሬዎስ ለዚያች ከተማ ሌላ በረከት ይዞ መጣ። በወረሃ ጥር በ25ኛው ቀን አጅባር ትጨነቃለች፣ ደብረታቦር በደስታ ትዘላለች፣ ሊቃውንቱ ይዘምራሉ፣ ያሸበሽባሉ፣ ያጨበጭባሉ፣ ፈረሰኞቹ ሽምጥ ይጋልባሉ። ጀግንነታቸውን ያሳያሉ። በዚያች ምድር የሚሆነውን ለማዬት የሄደው ሁሉ በእግሩ ጫፍ እየቆሞ በጉጉት ይመለከታል። በእግሩ ጫፍ ሆኖም ማዬት ያልቻ ረጅም ዛፍ እየመረጠ እየተሰቀለ ያያል። ያን የመሰለ ውብ ዝማሬ፣ ዕፁብ የሆነ ጉግሥ ማሳለፍ አይፈልግምና። ያን ሳያይ ቀረ ማለት ነብሱ ደስታን ስትሻ ከልክሏታል እንደማለት ነው።
በጥር 24 ቀን በመንበረ ንግሥት ልጅቱ ማርያም የሚገኘው መርቆሬዎስ ከመንበሩ ወጥቶ ወደ አጅባር ይወርዳል። አጅባር በእርግብ አምሳል መላዕክት መጥተው እንደሰፈሩበት ሁሉ ነጫጭ የለበሱ ምዕምናን ያለብሷታል። ምድሪቷን ያስውቧታል። የመርቆሬዎስ ዓመታዊ በዓል በደብረታቦር ደማቁ የጥምቀት በዓል ነው ይባላል። ይህ በዓል በተሸለሙ ፈረሶች ወኔ በሚተናነቃቸው ጋላቢዎች ደምቆ ይውላል። በዓሉ በፈረስ እየታጀበ እፅብ እያስባለ መከበር ከጀመረ 72 ዓመታት ማስቆጠሩን በደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ሰብሳቢ ዲያቆን ይብልጣል አድማሴ ነግረውኛል። ነገር ግን ታቦቱ ከዚያ በፊትም ይወጣ ነበር ነው ያሉኝ። ለዚህ ድንቅ በዓል ከአንድ ወር በፊት ጀምሮ ዝግጅት እንደሚደረግም ስምቻለሁ።
ቀኑ ሲደርስ የተንጣለለው ሜዳ ነጭ መብሩቅ የለበሰ ይመስላል፡፡ የበዓለ መርቆሬዎስ አጅባርን ያዬ ሁሉ ነገሥታቱ ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት ብለው ሠራዊታቸውን ያንቀሳቅሱ ይመስላል። ጦርና ጋሻው በላይ የሚደረገው የፈረሰኛ ልብስ ሁሉ የቀደመውን ዘመን መልሶ ያሳያል። ሽምጥ ግልቢያው ሲጀመር የሀገሬው ኃያል ሠራዊት ጠላትን ድባቅ እየመታ ያለ ይመስላል። ትይንቱ ልዩ ነው። የበረታው ሲማታ የደከመው ሲመታ ሲታይ አጀብ ያሰኛል። የሀገሬውን ፈረሰኛ እያዩ መይሳው ከእነ ገብርዬና ከባለሟሉቹ ጋር ሲያደርግ የነበረው ሁሉ በትዝታ ይመጣል። ያን ዘመን ያዩት ይመስላል።
ታቦተ መርቆሬዎስ በደንኳኑ ያርፋል። ፈረስ ጉግሱ ሳይደራ፣ ሰውና መላዕክት፣ ሰውና እግዚአብሔር ሳይደሰቱ ታቦቱ አይነሳም። ፈረሰኛው መርቆሪዮስን በፈረስ ለማስደሰት የወደደው የሀገሬው ሰው ፈረሱን እየሸለመ፣ ዘንጉን እያመቻቸ በጠዋት ይመጣል። አጅባርን ያስጨንቃታል። ሀጅ ባሕር ከሚለው ስያሜውን እንደወሰደ የሚነገርለት አጅባር ሜዳ አብሮ ሽምጥ የሚጋልብ ይመስላል። ያን ትዕይንት ያዬ ሁሉ መንፈሱ ትታደሳለች፣ ሀሴትም ታደርጋለች።
ጉግሡ ሲጠናቀቅ አስቀድሞ የሰበሰባቸውን ታቦት ይከባሉ። ፈረሰኛው በፈረስ፣ እግረኛው በሆታና በልልታ ያጅቡታል። አብዝተው እያመሰገኑ ወደ ማደሪያው ይመልሱታል። ዲያቆናቱ ሰማያዊ የሚመስል ዝማሬ ያደርጋሉ። ከበሮው ይቆረቆራል። ፅሕናው ይፀነፀናል፣ ወረብ ይወረባል። ዝማሬ ይደረሳል። ምድር ትደሰታለች። ሰማይ መልካሙን ትመለከታለች።
ምን አልባትም ከኢትዮጵያ ውጭ እንዲህ አይነት ነገር የሚገኝ አይመሰልም። አለባበሱ፣ አጨፋፈሩ ሁሉም ባሕላዊ ነው። በዚህ በዓል ከአራት መቶ እስከ አምስት መቶ ፈረሰኞች ይታደሙበታል። እነዚህ ሁሉ ሰብሳቢያቸውን ታቦት ወደማደሪያው ሳያስገቡ አይለያዩም። ጨዋታው መተዛዘኑ ሁሉም ልዩ ነው።
ኢትዮጵያን አብዝቶ ላያት ሁሉ አንቺስ ድንቅ ነሽ፣ እንከንም የለሽ ማለቱ አይቀርም። የሰማይን በምድር የምትሠራ፣ የፈጣሪዋን ስም አብዝታ የምትጠራ፣ በማንነቷ የምትኮራ፣ የምድርን ችግርና ፈተና የማትፈራ፣ በመልካም ምድር መልካም ፍሬ የምታፈራ ኢትዮጵያ ናት። የተወደደውን ሁሉ ታደርጋለች። የተጣለውን ሁሉ ታስወግዳለች። በጉያዋ የያዘቻቸው ሁሉ እፁቦች ናቸው። እነሆ ዓለም ይፈልጋታል። እንዲያገኛትና የውስጧን እንዲወስድ ሁሉ ይሻል። ዳሩ ግን ጠባቂዋ ሚስጥር፣ አፈጣጠሯ ዥንጉርጉር ነውና አይቻላቸውም። ስለ ኢትዮጵያ መልካም ልብ ያላቸው ያደንቃሉ። ክፍሉ ልብ ያላቸውም ይወድቃሉ። የማይሸነፈውን ይዛለችና የሚያሸንፋት የለም።
ደግነቱ ዘላለም የሚፈስስ እንጂ የማይነጥፈው የቤጌምድር ሰው ስሞት ብሎ እያጎረሰ፣ የራሱን አውልቆ እያለበሰ፣ ለሥጋ ረሃብ እያረሰ፣ ለመንፈስ ረሃብ እየቀደሰና እያስቀደሰ፣ ወገን ሲደፈር እየተኮሰ ሀገር በክብሯ እንድትፀና ያደርጋል።
ታዲያ ይህ ውብ በዓል ታላቅ ሆኖ ሳለ በታላቁ አልታወቀም። የበዓሉ ባለቤት ቤተክርስቲያን እንቁውን ብትይዘውም ለሰው አላስተዋወቀችውም። በዓላት ወደ መንግሥት ይሄዳሉ እንጂ መንግሥት ወደበዓላት መጥቶ አያስተዋወቅም ነው ያሉኝ ዲያቆን ይበልጣል።
የደቡብ ጎንደር ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ከደብረታቦር ከተማ አስተዳደርና ከደብረታቦር ዩኒቨርስቲ ጋር በመሆን በዓሉ ባህላዊ ይዘቱን እንደጠበቀ በዓለም አቀፈ ደረጃ በቅርስነት እንዲመዘገብ አልሞ እየሰራ መሆኑን በመምሪያው የቅርስ ምዝገባ ባለሙያው ሰለሞን ካሳው ተናግርዋል፡፡
በዚህቺው ከተማ ሌላ ቅርስም አለ። በደብረታቦር መድኃኔዓለም በቴዎድሮስ እጅ የተሠራ የደወል ቤት አለ። የንጉሡ መኖሪያና የችሎት ሥፍራም በዚሁ ይገኛል። ደብረታቦር ብዙ ያላት ግን ጥቂትም ያልተባለላት። ዕልፍ ሀብት ያላት ጥቂትም ያልታየላት ናት ደብረታቦር። ልዩ ነው አርሱስ ፈረሰኛው መርቆሬዎስ ሲነግሥ። ይሂዱ ይዩት የማይረሳ ትዝታ፣ ወሰን የሌለው እርካታ፣ ልክ የሌለው ደስታ ያገኙበታል። እንኳን ለመርቆሬዎስ ዓመታዊ ክብረ በዓል አደረሳችሁ።
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ