
መድኃኒትነት ያላቸውን ዕጽዋት በሳይንሳዊ መንገድ በማዘጋጀት ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየሠራ መሆኑን ዩኒቨርሲቲው አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር ፡ ጥር 24/2013 ዓ.ም (አብመድ) የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ሀገር በቀል እውቀቶችን ጠብቆ በማቆየትና ሳይንሳዊ የአሠራር ሂደትን በመከተል ፈዋሽነታቸው የተረጋገጠ መድኃኒቶችን ጥቅም ላይ ለማዋል እየሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ቀደምት ኢትዮጵያውያን ለመድኃኒትነት ሲጠቀሙባቸው የነበሩ በርካታ ዕጽዋትን ለመጠበቅ፣ ለማላመድና በተለያየ ሥነ-ምሕዳራዊ ቀውስ ምክንያት ዝርያቸው እንዳይጠፋ ለመታደግ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ነው ዩኒቨርሲቲው ያስታወቀው፡፡
የመድኃኒታዊ ዕጽዋትና ብዝሃ-ሕይወት ማዕከል በማቋቋምም በሰሜን ሸዋ ዞን የት ቦታ፣ ምን አይነት መድኃኒታዊ ዕፅዋት እንደሚገኙ፣ ለምን አይነት ሕመም ፈዋሽ እንደሚሆኑና ያሉበት ደረጃ በጥናት ተለይቷል፡፡ በተለይም የአካባቢውን 10 አንገብጋቢ በሽታ በሚፈውሱ እጽዋት ላይ ትኩረት መደረጉን በዩኒቨርሲቲው መድኃኒታዊ ዕፅዋትና ብዝሃ ሕይወት እንክብካቤ ማዕከል ዳይሬክተር አማረ አያሌው (ዶክተር) ገልጸዋል፡፡
ለዚህም በ2008 ዓ.ም የአንኮበር መድኃኒታዊ ዕፅዋት ቅመማና ብዝሃ ሕይወት እንክብካቤ ፕሮጀክትን አቋቁሞ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው ብለዋል፡፡
ዳይሬክተሩ እንዳሉት አንኮበር ለረጂም ዘመናት የነግሥታት መቀመጫ ስለነበረች በአካባቢው በከፍተኛ ደረጃ የባሕል ሕክምና ይሰጥ ነበር፡፡ የሁሉም አየር ንብረት ባለቤት መሆኗም መድኃኒታዊ ዕጽዋትን ለማልማት ምቹ ያደርገዋል ነው ያሉት፡፡
በአንኮበር መድኃኒታዊ ዕፅዋት ቅመማና ብዝሃ ሕይወት እንክብካቤ ማዕከል ከ130 በላይ ፈዋሽነት ያላቸው የዕጽዋት ዝርያዎችን አልምቷል፡፡ ጫካ ውስጥ የሚገኙ ዕጽዋት ደኀንነታቸው እንዲጠበቅም እየተሠራ ነው፡፡ መድኃኒታዊ ዕጽዋቱ በዘመናዊ መልኩ ተዘጋጅተው ጥቅም ላይ እንዲውሉም የተለያዩ ደረጃዎችን የለፈ የምርምር ሥራ ተከናውኗል፡፡
ሳይንሳዊ ሂደቱን ተከትሎ ውጤት ለማግኘት 15 ዓመታት መሥራት ቢጠይቅም ከተቋቋመ ጀምሮ አምስት መድኃኒታዊ ዕጽዋትን ለሙከራ ማብቃቱን ዳይሬክተሩ አማረ አያሌው (ዶክተር) አስታውቀዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በቴክኒካዊ ግምገማ ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
በአጭር ጊዜ ውጤቱ በመገኘቱም ለዩኒቨርሲቲው ትልቅ ስኬት መሆኑን ያነሱት ዶክተር አማረ ‘ኢንክሪዚንክ ፒውፕል ኦፖርቹኒቲ’ የተሰኘ የጣልያን ድርጅት በዘርፉ ሢሠራ መቆየቱን እና ያለብዙ ውጣ ውረድ ዕጽዋት ማግኘት መቻሉን በመልካም አጋጣሚነት ጠቅሰዋል፡፡
የሙከራ ውጤቱን ተከትሎ የሚያስፈልጉ ማሻሻያዎችን በመጨመርም አገልግሎት ላይ እዲውሉ በትኩረት ይሠራል ብለዋል፡፡
ማኅበረሰቡ ዕጽዋቱን ማልማት እንዲችል ተግባር ተኮር ስልጠና እንደሚሰጥም ጠቅሰዋል፡፡ ደኀንነቱና ፈዋሽነቱ የተጠበቀ መድኃኒት ለማግኘት የሚፈጀውን ጊዜ ለማሳጠርም ከባሕል መድኃኒት አዋቂዎች ጋር በትብብር እንደሚሠራ ዶክተር አማረ አስገንዝበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ