“ከተሞች በመሰረተ ልማትና በኢንቨስትመንት እንዲጠናከሩ የክልሉ መንግስት ከምንጊዜውም በላቀ ትኩረት እየሰራ ነው” የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር

305
“ከተሞች በመሰረተ ልማትና በኢንቨስትመንት እንዲጠናከሩ የክልሉ መንግስት ከምንጊዜውም በላቀ ትኩረት እየሰራ ነው” የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር
ባሕር ዳር፡ ጥር 24/2013 ዓ.ም (አብመድ) በሰሜን ወሎ ዞን በዋድላ ወረዳ ስር የነበረችው ጋሸና ከተማ ወደ ከተማ አስተዳደርነት አድጋለች። የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኀንነት አማካሪ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው፣ የስትራቴጅክ ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር በሚኒስትር ማዕረግ አቶ ዮሐንስ ቧያለውን ጨምሮ የክልልና የፌዴራል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት የከተማ አስተዳደርነት ይፋ ማድረጊያ መርሐ ግብር ተከናውኗል።
ጋሸና ከተማ ከወረታ፣ ወልድያና ከዓለም ከተማ ላልይበላ መንገድ መገናኛ ናት። የከተማዋ ነዋሪዎች እንዳሉት ከተመሰረተች ከ20 ዓመታት የማይበልጣት ጋሸና ከተማ በማህበራዊ ተቋማትና በኢንቨስትመንት እያደገች መጥታለች። ጠንካራ የስራ ባህልን በመገንባት የትራንስፖርት መዳረሻነቷን ወደ ተጠቃሚነት እያሳደጉ መሆናቸውንም ለአብመድ ተናግረዋል።
የጋሸና ከተማ ስራ አስኪያጅ አቶ መላኩ ወረታ የሃይማኖታዊና ታሪካዊ ሐብቶች መዳረሻ የሆነችው ጋሸና ከተማ ወደ ከተማ አስተዳደርነት ማደጓ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግና የቱሪስት መዳረሻነቷን ለማጉላት አጋዥ እንደሚሆን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው የክልሉ መንግስት የከተሞችን እድገት ለማጠናከርና የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የደረጃ ሽግግርን ተግባራዊ እያደረገ ስለመሆኑ አንስተዋል። ጋሸና ከተማ በክልሉ ካሉ ስትራቴጅክ የእድገት ማዕከላት መካከል እንዷ ናት ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ከተሞች በኢንቨስትመንትና በመሰረተ ልማት እንዲጠናከሩ ከምንጊዜውም በላቀ ትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የአካባቢው ህዝብም መንግስት ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን በታማኝነት ግብር በመክፈልና የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ አጋርነቱን ማጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል።
ዘጋቢ፡- ስማቸው እሸቴ – ከጋሸና
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበአብሮነት የደመቀው ኢትዮጵያዊነት
Next articleመድኃኒትነት ያላቸውን ዕጽዋት በሳይንሳዊ መንገድ በማዘጋጀት ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየሠራ መሆኑን ዩኒቨርሲቲው አስታወቀ፡፡