መንግሥት የከተሞችን የወደፊት ዕድገት ያገናዘበ መሠረተ ልማት ሊያሟላ እንደሚገባ የወገዳ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ።

447
መንግሥት የከተሞችን የወደፊት ዕድገት ያገናዘበ መሠረተ ልማት ሊያሟላ እንደሚገባ የወገዳ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ።
ባሕር ዳር፡ ጥር 24/2013 ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል ከገጠር ወደ ከተማ የሚፈልሰው ህዝብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ የከተሞችን ኢንቨስትመንት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራን እና የመሰረተ ልማት አቅርቦትን ለማስፋፋት የክልሉ መንግስት እየሠራ ይገኛል። በዚህ ዓመት ብቻ 30 ከተሞችን ወደ ከተማ አስተዳደርነት ማሳደጉም የዚህ አንዱ ማሳያ ነው።
ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 3 ከተሞች በደቡብ ጎንደር ዞን የሚገኙ ሲሆን የወገዳ ከተማም ጥያቄው ከተመለሰላቸው ውስጥ አንዷ ሆናለች፡፡ የወገዳ ከተማ በ1975 ዓ.ም የተቆረቆረች ሲሆን ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ በመሪ መዘጋጃ ቤት ስትመራ ቆይታለች። ከ35 ሺህ በላይ ህዝብ እዳላት የሚገመተው የወገዳ ከተማ ወደ ከተማ አስተዳደርነት ማደጓን አስመልክቶ እና አጠቃላይ የከተማዋን ልማት በተመለከተ የክልል እና የዞን የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የጎንደር እና የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች በተገኙበት ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ የወገዳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አስናቀው ቆየው የከተማ አስተዳደሩ አካባቢው ለገበያ ትስስር፣ ለመሠረተ ልማት መፋጠንና ለኢንቨስትመንት መሥፋፋት ትልቅ አቅም እንዳለው ገልጸዋል። አካባቢው በቀደመው ጊዜ ለነገስታት ሳይቀር ወደ አዲስ አበባ ይላክ እንደነበር የሚነገርለት “ስይት” እየተባለ የሚጠራው ነጭ ጤፍ እና ሌሎች ሀብቶች ባለቤት በመሆኑ በልማት ለሚሰማራ ባለሃብት ትልቅ አቅም እንዳለው ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት በመሠራት ላይ የሚገኘው የአስፓልት መንገድ ከወሎና ከጎጃም ጋር በመገናኘት ከተማዋን እና አካባቢውን የልማት ኮሪደር ያደርገዋል ብለዋል።
የወገዳ ከተማ በመሠረተ ልማት አለመሟላት ከባንክ የሚፈልጉትን ብድር ማግኘት አለመቻላቸውንም ነዋሪዎቹ በውይይቱ አንስተዋል። የመንገድ፣ የውኃ፣ የመብራት እና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን በተሟላ መንገድ ማግኘት አለመቻላቸውንም ጠቅሰዋል። በእነዚህ ችግሮች የተነሳ ባለሃብቶች አካባቢያቸውን እንዳያለሙ ትልቅ ችግር ሆኖ መቆየቱንም ነግረውናል።
ከተማዋ ወደ ከተማ አስተዳደርነት ማደጓ እነዚህን ችግሮች ለመፍታትና ለአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል። በመሆኑም መንግሥት የከተሞችን የወደፊት ዕድገት ያገናዘበ መሠረተ ልማት ማሟላት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባው ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበኩር ጋዜጣ ጥር 24/2013 ዓ/ም ዕትም
Next articleየሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች ማህበርን በዩኒስኮ ለማስመዝገብ እየተሠራ ነው፡፡