
ባለፉት 6 ወራት 9 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 23/2013 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የ2013 በጀት ዓመት የ6 ወራት የገቢ አሰባሰብና በሌሎች ተግባራት አፈጻጸም ዙሪያ በየደረጃው ከሚገኙ የተቋሙ ባለድርሻ አካላት ጋር በባሕር ዳር የግምገማና የክለሳ ፕሮግራም እያካሄደ ነው፡፡
የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኀላፊ ወይዘሮ ብዙአየሁ ቢያዝን በበጀት ዓመቱ 20 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት 9 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ እንደተቻለም ተናግረዋል፡፡
አፈጻጸሙ በግማሽ ዓመቱ መሰብሰብ ከሚገባው 92 ነጥብ 4 በመቶ ድርሻ ያለው ሲሆን በበጀት ዓመቱ መሰብሰብ ከሚገባው አንጻር ግን 46 በመቶ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በቀጣይ 6 ወራት የክልሉን ገቢ የመሰብሰብ አቅም ለማሳደግ በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካለት በትኩረት እንዲሰሩም ኀላፊዋ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ በተለያዩ የገቢ አርዕስቶች ገቢ እየሰበሰበ ሲሆን የከተማ አገልግሎት ገቢ አንዱ ነው፡፡ በ2013 በጀት ዓመት ከከተማ አገልግሎት ገቢ 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ እቅድ ተይዟል፡፡ በ6 ወራት ውስጥም 906 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ገልጿል፡፡
በግማሽ ዓመቱ በርካታ የክልሉ ከተሞች የቦታ ሊዝ ሽያጭ ጨረታ ባለማውጣታቸው ገቢው እንዲቀንስ ምክንያት መሆኑም ተጠቅሷል፡፡ በአማራ ክልል ውስጥ የሚገኙ በርካታ ከተሞች ቦታ በሊዝ የሚያስተላልፉ ቢሆንም ገቢ በመሰብሰብ በኩል ግን ችግር የሚታይበት ሆኖ ቆይቷል ነው የተባለው፡፡
የችግሩ ምንጭ ደግሞ ማዘጋጃ ቤቶች ሊዝ ያስተላለፉበትን መረጃ ለገቢ ተቋሙ ባለማስተላለፍ፣ የጨረታ አሸናፊዎች ክፍያ ለመፈጸም በተቀመጠው ጊዜ ሳይተገብሩ ሲቀሩ የሚመለከተው ተቋም ካርታውን የማምከን ሥራ ባለመሥራቱ ገቢው በአግባቡ እንዳይሰበሰብ እንዳደረገው ተገልጿል፡፡ የክልሉ ገቢዎች ቢሮ የከተማ አገልግሎት ገቢ በአግባቡ እንዲሰበሰብ በተያዘው ዓመት ልዩ ትኩረት እንደሰጠም ተጠቅሷል፡፡
በአማራ ክልል በ2013 በጀት ዓመት በግማሽ ዓመቱ በተገኘው 9 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ገቢ ታማኝ ግብር ከፋዮች እና በየደረጃው የሚገኙ የተቋሙ ሙያተኞች ሚናቸው የላቀ እንደነበር ቢሮው አንስቷል፡፡ በሌላ በኩል አሁንም ያለደረሰኝ ሽያጭ የሚፈጽሙ፣ በሀሰተኛ ደረሰኝ ሽያጭ የሚያከናውኑ፣ ግብር የሚሰውሩ ግብር ከፋዮች በ6ወሩ ውስጥ መታየቱን አስታውቋል ቢሮው፡፡
በግብር ማጭበርበር እና በሌሎች ተገቢ ባልሆኑ ተግባራት ተሳታፊ የነበሩ ግብር ከፋዮች እና ባለሙያዎች ላይ እርምጃ መወሰዱንም ቢሮው ገልጿል፡፡
ዘጋቢ፡- ተመስገን ዳረጎት
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ