የላይኛው ርብ የመስኖ ፕሮጀክት ግንባታ በታቀደለት ፍጥነት እንዲጠናቀቅ በቅንጅት ሊሠራ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

327
የላይኛው ርብ የመስኖ ፕሮጀክት ግንባታ በታቀደለት ፍጥነት እንዲጠናቀቅ በቅንጅት ሊሠራ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 23/2013 ዓ.ም (አብመድ) በአሁኑ ወቅት 21 በመቶ መድረስ የነበረበት የላይኛው ርብ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ግንባታ አፈጻጸሙ 10 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ እተገነባ ያለው በደቡብ ጎንደር ዞን ከ12 ሺህ በላይ የሊቦ ከምከምና የፎገራ ወረዳ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቦ ነው፡፡
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ከ6 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የሚያለማው ይህ ፕሮጀክት ከፌዴራል መስኖ ልማት ኮሚሽን 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በጀት ተመድቦለት ግንባታው በአማራ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ነው እየተከናወነ የሚገኘው፡፡
ፕሮጀክቱ ሰኔ/2011 ዓ.ም ውል ተይዞለት ግንባታው ጥር/2012 ዓ.ም ተጀምሯል፡፡ የሠራተኛ ካምፖችና ቢሮዎች፣ የአናት ሥራ፣ የመጀመሪያ ቦይ፣ ወደ ፎገራና ሊቦከምከም ወረዳዎች የሚሠሩ ቦዮችና በርካታ የመስኖ ልማት አውታሮች የግንባታው አካል ናቸው፡፡ የአማራ ዲዛይንና ቁጥጥር ሥራዎች ድርጅትም ግንባታውን የማማከርና የመቆጣጠር ተግባር ተሰጥቶታል፡፡ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቱ ግንባታ መጓተቱን አማካሪዉ መሃንዲስ ጌታቸው ከፍያለው ተናግረዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ መሬት ከሦስተኛ ወገን ነጻ አለመደረጉ እንደሆነ በምክንያትነት አንስተዋል፡፡
እንደ አቶ ጌታቸው ማብራሪያ ግንባታው የሚያርፍባቸው ቦታዎች በሙሉ የይዞታ መሬት ናቸው፡፡ ግንባታው የሚያርፍበት የይዞታ መሬት በሚመለከተው ተቋም ከሦስተኛ ወገን ነጻ አለመደረጉ ለሥራው መጓተት ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም በማኅበረሰቡ ውስጥ ቅሬታ በመፈጠሩ ሙሉ የሥራ ማሽን ይዞ ወደሥራ መግባት እንዳልተቻለ አስረድተዋል፡፡
በዚህም ምክንያት 21 በመቶ መድረስ የነበረበት የግንባታ አፈጻጸም በአሁኑ ወቅት 10 በመቶ ብቻ ሆኗል፡፡ እስከ ሰኔ 30/2013 ዓ.ም ድረስ የግንባታ ሥራው 39 በመቶ መድረስ ይጠበቅበታል ብለዋል አቶ ጌታቸው፡፡
የፕሮጀክቱ ኀላፊ ኤርሚያስ እምሬ በጉዳዩ ላይ ተመሳሳይ ሀሳብ ሰንዝረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅም ችግሮች በፍጥነት እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡
የአውስኮድ የሥራ አመራር ቦርድ አባላትና የድርጅቱ ማኔጅመንት አባላት የፕሮጀክቱን የሥራ ሁኔታ የመስክ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ በጉብኝታቸውም የካሳ ክፍያ፣ ጥራት ያለው የግንባታ ድንጋይና አሸዋ በአካባቢው መጥፋት፣ የክሬሸር ሳይት የካሳ አፈጻጸምና የቅየሳ መሳሪያ ችግር መኖራቸውን ተገንዝበዋል፡፡
በተለይ የካሳ ክፍያ ጉዳይ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እንዳስነሳ ተመላክቷል። ከመስክ ምልከታ በኋላ ባለድረሻ አካላት ባደረጉት ውይይት በተቋራጭ፣ በአማካሪ ድርጅትና በአሠሪ ተቋም መካከል ቅንጅታዊ አሠራርና ውጤታማ ተግባቦት አለመኖሩን አንስተዋል፡፡ ይህም ችግሮች እንዳይስተካከሉ ምክንያት እንደሆነ ነው የተጠቀሰው፡፡ ችግሮቹ በፍጥነት እንዲፈቱ አቅጣጫ እንደሚቀመጥም ነው የተገለጸው፡፡
የሥራ አመራር ቦርዱ ሰብሳቢ ጎሹ እንዳላማው በአውስኮድ በኩል የተነሱ ችግሮች ተስተካክለው በሙሉ አቅሙ እንዲሠራ ይደረጋል ብለዋል፡፡ በካሳ አከፋፈል በኩል የተነሱት ክፍተቶች እንደሚስተካከሉ ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የመሠረተ ልማት አማካሪ መስፍን አበጀ ለፕሮጀክቱ መጓተት ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ተወቃሽ አድርገዋል፡፡ የክልሉ መንግሥትም ሦስቱን ተቋማት በማቀናጀት ችግሩ እንዲስተካከል ያደርጋል ብለዋል፡፡ ከሁሉም በላይ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ በፍጥነት የካሳ ሥራውን እንዲያጠናቅቅ ማድረግ ቀዳሚ የመፍትሔ ሀሳብ መሆኑን አቶ መስፍን አብራርተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበየዓመቱ የሚከበረውን የአገው ፈረሰኞች ማኅበር በዓልን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን የብሔረሰብ አስተዳደሩ ዋና አስተዳዳሪ ተናገሩ፡፡
Next articleባለፉት 6 ወራት 9 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ፡፡