
18ኛው የመላው ደቡብ ወሎ ዞን የባህል ስፖርት ውድድርና 14ኛው የባህል ፌስቲቫል በለጋምቦ ወረዳ አጠቃላይ አሸናፊነት ተጠናቀቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 23/2013 ዓ.ም (አብመድ) ውድድሩ ለመላው አማራ የባህል ስፖርት ውድድር ዞኑን የሚወክሉ ስፖርተኞችን ለመምረጥ ማስቻሉም ተገልጿል፡፡ በለጋምቦ ወረዳ አስተናጋጅነት ላለፉት ዘጠኝ ቀናት ሲካሄድ የነበረው 18ኛው የደቡብ ወሎ ዞን የባህል ስፖርት ውድድርና 14ኛው የባህል ፌስቲቫል ተጠናቋል፡፡ በውድድሩ መጠናቀቂያ ዕለት በትግል ወንዶችና ሴቶች ለጋምቦ ወረኢሉን በሁለቱም ፆታ በማሸነፍ የወርቅ ሜዳልያ አግኝቷል፡፡
በገና ጨዋታ ደግሞ ሳይንት አስተናጋጁ የለጋምቦ ወረዳን በመለያ ምት 3ለ2 በማሸነፍ የዋንጫ ባለቤት ሆኗል፡፡ በውድድሩ ከ22 ወረዳዎች የተውጣጡ ከ1 ሺህ 500 በላይ ተወዳዳሪዎች የተሳተፉ ሲሆን በ10 የባህል ስፖርት ዓይነቶችም ሲፎካከሩ ቆይተዋል፡፡
በውድድር ቆይታቸውም የእርስ በርስ ግንኙነታቸውን ከማጠናከር ባለፈ ለባህሉ እድገት የጎላ ሚና እንዳለው የውድድሩ ተሳታፊዎች ለአብመድ ተናግረዋል፡፡
ውድድሩን ላዘጋቸው ለለጋምቦ ወረዳም ምስጋና ያቀረቡት ተሳታፊዎቹ በአቀስታ ከተማ የነበራቸው ቆይታ አይረሴ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ውድድሩ በመጪው የካቲት ኮምቦልቻ ከተማ ላይ ለሚደረገው የመላው አማራ የባህል ስፖርት ሻምፒዮና ስኬታማነት ከፍተኛ ልምድ የተቀሰመበት መሆኑን የገለጹት ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን ስፖርት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት የባህል ስፖርት ቴክኒካል አማካሪ አቶ አለማየሁ ይርጋ ናቸው፡፡
በውድድሩ ማጠናቀቂያ መድረክ ላይ የተገኙት የደቡብ ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ሱለይማን እሸቱ የባህል ስፖርት የአንድን አካባቢ ትውፊት ወደ ሌላው አካባቢ ለማወራረስና ያልተበረዙ ማንነቶችን ለማንጸባረቅ ምቹ አጋጣሚ የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡ ውድድሮች እሴታቸውን ጠብቀው እንዲከናወኑ ከዞኑ ስፖርት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ጋር በጋራ እየሠሩ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
18ኛው የደቡብ ወሎ ዞን የባህል ስፖርት ውድድርና 14ኛው የባህል ፌስቲቫል በሠላም የተጠናቀቀ ቢሆንም የትግል መወዳደሪያ ፍራሽ ምቹ አለመሆን ተወዳዳሪዎችን ለጉዳት ሲዳርግ አብመድ ታዝቧል፡፡ ተመሳሳይ ችግር በመላው አማራ የባህል ስፖርት ውድድር ላይ እንዳይከሰት ምን ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነም የዞኑን ስፖርት ተጠሪ ጽሕፈት ቤትን ጠይቋል፡፡
የዞኑ ስፖርት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገላግለው ተሾመ በበኩላቸው በዚህ ውድድር ተሳታፊ ከነበሩ ተወዳዳሪዎች መካከል ለመላው አማራ የባህል ስፖርት ውድድር ዞኑን የሚወክሉ ስፖርተኞችን መምረጣቸውን ገልጸው በዚህ ውድድር ላይ የተስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
18ኛው የመላው ደቡብ ወሎ የባህል ስፖርት ውድድርና 14ኛው የባህል ፌስቲቫል ሲጠናቀቅም የደላንታ ወረዳ 3ኛ፣ ወረባቦ ወረዳ ሁለተኛ፣ የለጋምቦ ወረዳ አንደኛ ሆነው ጨርሰዋል፡፡ ለተወዳዳሪ ወረዳዎችና ተሳታፊ ስፖርተኞችም የሜዳልያና የዋንጫ ሽልማት ተሰጥቷል፡፡
ዘጋቢ፡- አሊ ይመር – ከአቀስታ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ