አቶ ደመቀ መኮንን የአዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር አካላት በተገኙበት መድረክ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ማብራሪያ ሰጡ፡፡

366
አቶ ደመቀ መኮንን የአዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር አካላት በተገኙበት መድረክ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ማብራሪያ ሰጡ፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 22/2013 ዓ.ም (አብመድ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አትላንቲክ ካውንስል የተሰኘ የአሜሪካ ቲንክ-ታንክ ተቋም ባዘጋጀው የበይነ መረብ መድረክ ላይ በመሳተፍ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ለተሳታፊዎች ገለፃ ሰጥተዋል።
በውይይቱ ላይ የአሜሪካ የኮንግረስ አባላት እና የአዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር አካላት ተሳትፎ አድርገዋል።
ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጋር ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበሳይ በውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል።
አቶ ደመቀ መኮንን ለተሳታፊዎች ያደረጉት ገለፃ በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ፣ በክልሉ የሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ የሚደረግ ርብርብ፣ የመልሶ ማቋቋም፣ የህወሃት ቡድን ያፈራረሳቸው የመሰረተ ልማቶችን መልስ ግንባታ፣ በክልሉ እንቅስቃሴ ከማድረግ ጋር የሚነሳ ጥያቄ እና በክልሉ የሰብአዊ መብት ጥበቃ በተመለከተ የሚነሱ ክሶች፣ በትግራይ ክልል ባሉ የመጠልያ ጣቢያዎች የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ሁኔታ እንዲሁም በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነበር።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገለፃቸው የህወሃት ቡድን በትግራይ ክልል ባለው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ አስነዋሪ ጥቃት በመፈፀም የተገባበት የህግ ማስከበር ዘመቻ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ዘመቻውንም በአጭር ጊዜ ውስጥ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን ገልፀው፣ ከዘመቻ በኋላ በክልሉ መረጋጋት ለማስፈን፣ ዘመቻው ከመካሄዱ በፊት በሴፊትኔት የድጋፍ ማዕቀፍ የሚረዱ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሰዎች ሰብአዊ ድጋፍ የማድረስ እንዲሁም በተፈጠረው ሁኔታ የሰብአዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ተጨማሪ ሰባት መቶ ሺህ ሰዎች ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርስ ለማድረግ በተሰራ ሥራ ለ1 ሚሊዮን 46 ሺህ ሰዎች የሰብአዊ እርዳታ ማድረስ ማቻሉን ገልጸዋል።
በአንዳንድ አካላት ሪፖርት የሚቀርብና በክልሉ የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ ፈላጊዎች 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ተብሎ የሚቀርበው በተጨባጭ መረጃ ላይ ያልተመሰረተ መሆኑንም ገልፀዋል።
አቶ ደመቀ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ስለሁኔታው መገንዘብ ያለበትን እውነታን አጽኖት በመስጠት አስረድተዋል።
በዋናነት የህወሃት ቡድን በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ እና በማይካድራ የፈፀመው ኢ ሰብዓዊ ድርጊት፣ በመሰረተ ልማቶች ላይ ያደረሰው ውድመት የሰብአዊ ድጋፎች ለማድረስ የፈጠረው ጫና፣ በመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ ጁንታው የፈፀመው የማፍረስ እርምጃ የተለያዩ አገልግሎቶች ላይ መቋረጥ አስከትሏል ነው ያሉት።
በዜጎች ላይ የተፈጠረው አስቸጋሪ ሁኔታን በአጠቃላይ በክልሉ የፈጠረው ውስብስብ ችግር የህወሃት ቡድን ሆነ ብሎ የፈጠረውና ከዚያ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት በመፈለጉ ነው ብለዋል።ያም ሆኖ ቡድኑ በአጠረ ጊዜ ተሸንፎ ለህግ ተጠያቂነት በመቅረብ ላይ መሆኑንም ገልፀዋል።
ከኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጉዳይ አንፃር ያለውን እና ኢትዮጵያ ጉዳዩን ለመፍታት ያላት አቋም በግልፅ የተቀመጠ መሆኑንም አስረድተዋል።
ኢትጵዮያ ከጎረቤት ሀገር ሱዳን ጋር ወደ አላስፈላጊ ግጭት መግባት እንደማትፈልግ፣ ለዚህም ጉዳዩ በሰላማዊ መንገድና በድርድር እንዲፈታ ቁርጠኛ ነኝ ነው ያሉት።
ጉዳዮ ሁለቱም ሀገራት በጋራ ባቋቋሙት እና ሲሰራበት በቆየው የመፍትሄ ሂደት መሰረት ሊፈታ እንደሚችል ኢትዮጵያ እንደምታምን ፤ የድንበር ጉዳዩን ለመፍታት ወደ ድርድር ጠረጴዛ ለመመለስ ሱዳኖች በቅርብ ጊዜ ድንበር ጥሳ ገብታ ከያዘቻቸው ቦታዎች ሙሉ በሙሉ ለቃ መውጣት በቅድመ ሁኔታነት መቀመጡም ተገልጿል።
ምንጭ:- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ ጽሕፈት ቤት
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“በአሁኑ ዘመን በጅምላ ማሰብ ማለት ማሰቢያን ማከራየት ነው” የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና አርቲስት ታማኝ በየነ
Next articleየሚኒስትሮች ምክር ቤት በመደበኛ ስብሰባው የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ።