
የአውስኮድ የቦርድና የማኔጅመንት አባላት የላይኛው ርብ የመስኖ ልማት ፕሮጀክትን የግንባታ አፈጻጸምን ተመልክተዋል።
ባሕር ዳር፡ ጥር 22/2013 ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን በሊቦ ከምከም እና ፎገራ ወረዳዎች በርብ ወንዝ ላይ በመገንባት ላይ የሚገኘው የላይኛው ርብ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት 6 ሺህ 2 ሄክታር በማልማት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የሥራ ዕድል መፍጠርና ድህነትን መቀነስ የሚያስችል ፕሮጀክት እንደሆነ ታምኖበት ግንባታው ተጀምሯል።
የላይኛው ርብ የመስኖ መሬት ዝግጅት የወንዝ የመቀልበሻ ከፍታው 6 ነጥብ 5 ሜትር ሲሆን ርዝመቱ 40 ሜትር ነው።
በፌዴራል የመስኖ ልማት ኮሚሽን 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚደረግበት ፕሮጀክቱ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ከ12 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ ታምኖበታል።
የፕሮጀክቱ ሥራ የተጀመረው በ2012 ዓ.ም ነው። ፕሮጀክቱን በተቋራጭነት የሚሠራው አማራ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ሲሆን የአማራ ዲዛይንና ቁጥጥር ሥራዎች ድርጅት የማማከሩን ሥራ ያከናውናል።
የግንባታውን አፈጻጸም የአውስኮድ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት፣ የድርጅቱ ማኔጅመንት አባላት፣ የደቡብ ጎንደር ዞን የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የፎገራና የሊቦ ከምከም ወረዳ የሥራ ኃላፊዎች የመስክ ምልከታ አድርገዋል።
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ