
በሦስት ቀናት ውስጥ ከ270 ሺህ በላይ ሴቶች የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር መከላከያ ክትባት እንደወሰዱ የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 21/2013 ዓ.ም (አብመድ) ጤና ቢሮው ለ6 ቀናት እድሜያቸው 14 ዓመት ለሞላቸው ልጃገረዶች የመጀመሪያና ሁለተኛ ዙር የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር መከላከያ ክትባት ከጥር 17 እስከ 22 /2013 ዓ.ም እየሰጠ ነው፡፡ ክትባቱ በክልሉ በትምህርት ቤቶችና በጤና ተቋማት እየተሰጠ ይገኛል፡፡
ክትባቱን ሲወስዱ ካገኘናቸው ተማሪዎች መካከል በባሕርዳር ከተማ የዶና በርበር 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪ ሜሮን ሙሉጌታ አንዷ ናት። ከ6 ወር በፊት የመጀመሪያ ዙር ክትባት እንደወሰደች ገልጻለች፡፡ ክትባቱን ለሁለተኛ ጊዜ በትምህርት ቤታቸው በመሰጠቱ መከተቧን ነግራናለች፡፡
የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር አደገኛና ገዳይ በሽታ ቢሆንም በክትባት መከላከል እንደሚቻል ግንዛቤ እንደተፈጠረላቸውም ነው ተማሪ ሜሮን የተናገረችው፡፡
ሌላዋ አስተያየቷን የሰጠችንና ክትባቱን በትምህርት ቤቷ ግቢ ውስጥ ስትወስድ ያገኘናት ተማሪ እናትትሁን ሙላት የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር አሁን መከተባችን በበሽታው እንዳንያዝ የሚከላከል በመሆኑ ለኛ ጥሩ አጋጣሚ ነው ብላለች፡፡ ስለ ማህፀን በር ጫፍ ካንሰር በጤና ባለሙያወች ትምህርት እንደተሰጣቸውም ተናግራለች፡፡
ሲስተር ተዋበች ንጉሤ በባሕር ዳር ከተማ የዳግማዊ ምኒልክ ጤና ጣቢያ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያ ናቸው። በዶና በርበር 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር መከላከያ ክትባት ለልጃገረድ ተማሪዎች ሲሰጡ ነበር ያገኘናቸው። ክትባቱን ከመስጠታቸው በፊት ለተማሪዎቹ ግንዛቤ መፍጠራቸውን ጠቁመዋል።
ክትባቱ በታቀደው መልኩ እንዲሰጥ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ይጠይቃል ያሉት የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ አስተባባሪ አቶ ፋሲል ታየ ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ወላጆች እድሜያቸው 14 ዓመት የሞላቸዉን ሴት ልጆቻቸውን ክትባቱ በሚሰጥባቸው ቦታዎች በመውሰድ እንዲያስከትቧቸው ጠይቀዋል።
የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር መከላከያ ክትባት በሁሉም ትምህርት ቤቶችና ጤና ተቋማት እየተሰጠ እንደሚገኝ በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የክትባት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ወርቅነህ ማሞ አስረድተዋል። እስከ ጥር 19 ድረስ ከትባቱ ለ276 ሺህ ልጃገረዶች ተሰጥቷል ብለዋል፡፡
ክትባቱ እድሜያቸው 14 ዓመት ለሞላቸው ልጃገረዶች ብቻ እንደሚሰጥ ያስረዱት አቶ ወርቅነህ እስከ ጥር 22/2013 ዓ.ም ድረስ ያልተከተቡ ልጃገረዶች ክትባቱን እንዲወስዱም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ብሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ