
የመሬት ወረራ ሲፈፀም ኃላፊነታቸውን ባልተወጡ በየደረጃው ያሉ የሥራ ኃላፊዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
ቤቶችን በህገወጥ መንገድ እንዲገነቡና የጋራ መኖርያ ቤቶች ካለአግባብ እንዲሰጡ ያደረጉ አካላትን ለሕግ ለማቅረብ እየተሠራ ነው ተብሏል፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 21/2013 ዓ.ም (አብመድ) በአዲስ አበባ ከተማ በተፈፀመ የመሬት ወረራ እና ግንባታ ፣ በህገ ወጥ መንገድ በተያዙ የጋራ መኖሪያ ቤቶችና የቀበሌ ቤቶች ዙሪያ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ ዛሬ ማብራሪያ ተሰጥቷል።
የከተማ አስተዳደሩ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ጊዜያት እየሰፋ የመጣውን የመሬት ወረራ እና ህገወጥ ግንባታን ለማስቆም እና በዘርፉ የሚስተዋለውን ሥርዓት አልበኝነት ከምንጩ ለማድረቅ ጥናት ማካሄዱን አቶ ጃንጥራር ተናግረዋል።
በከተማዋ የመሬት ወረራ ሲፈፀም ኃላፊነታቸውን ባልተወጡ በየደረጃው የሚገኙ የሥራ ኃላፊዎች ላይ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዷል፤ በቀጣይም እርምጃው ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት አቶ ጃንጥራር።
ቤቶችን በህገወጥ መንገድ እንዲገነቡ እና የጋራ መኖርያ ቤቶች ካለአግባብ እንዲሰጡ ያደረጉ አካላትን ለሕግ ለማቅረብ አጠቃላይ የጥናቱን ግኝቶች ለጠቅላይ አቃቤ ሕግ እና ለፌዴራል ፖሊስ ምርመራ እንዲጀመር መደረጉን አቶ ጃንጥራር ጠቁመዋል።
አሁን ከተማ አስተዳደሩ ያሰጠናው ጥናት ሕዝብ የሰጣቸውን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው በሕገ ወጥ ተግባር ለሚሳተፉ የሥራ ኃላፊዎች ትምህርት የሚሆን ነው ያሉት አቶ ጃንጥራር አስተዳደሩ አጥፊዎች በሕግ እንዲጠየቁ ለማድረግ ቁርጠኛ አቋም መያዙን አስገንዝበዋል።
ከተማ አስተዳደሩ በቅርቡ አስጠንቶ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት ከ1 ሺህ 338 ሄክታር መሬት በህገወጥ መንገድ የተወረረ፣ ከ21 ሺህ በላይ የጋራ መኖርያ ቤቶች በህገወጥ መንገድ ተይዘው የተገኙ ፣ 322 ህንጻዎች ደግሞ ባለቤት አልባ መሆናቸውን በጥናቱ መለየቱንና ይህም ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ የነበረ መሆኑን በጥናቱ መካተቱን አቶ ጃንጥራር መግለፃቸውን የአዲስ አበባ ፕረስ ሴክሬታሪያት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አመላክቷል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ