
እውነተኛ የፌዴራሊዝም ሥርዓት መተግበር የሚያስችል ማዕከል እያቋቋመ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 21/2013 ዓ.ም (አብመድ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት የተለያዩ ተግባራት ቢያከናውንም በፌዴራል ሥርዓትና በሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት አረዳዱ የበለጸገ ማኅበረሰብ ከመፍጠር አንጻር ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅበት ይገለፃል፡፡ የፌዴራል ሥርዓት ለኢትዮጵያ መተኪያ የሌለው አማራጭ ቢሆንም እንደ ሀገር ያለው አረዳድና አተገባበር የተሳሳተ መሆኑም ይነሳል፡፡
በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ-መንግሥትና የፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኃይለየሱስ ታዬ እንዳሉት የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊ የሕዝብ ስብጥር በአግባቡ ማስተናገድ የሚቻለው እውነተኛ የፌዴራሊዝም ሥርዓትን በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጨምሮ ይህንን በአግባቡ የመረዳት ውስንነት መኖሩን አመላክተዋል፡፡ በዚህም በሀገሪቱ የፖለቲካ ውጥረትና አለመግባባት መፈጠሩን አንስተዋል፡፡ ችግሩን በመረዳት ባለፈው ዓመት የሕገመንግሥትና የፌዴራሊዝም አስተምሕሮ ማዕከል እንዲቋቋም ተወስኗል፡፡ ለዚህም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጅ መውጣቱን አስታውቀዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ችግሩን ለመፍታት የተጠናከረ የፌዴራሊዝም አስተምህሮ በመስጠት ሥርዓቱን በሚገባ መተግበር ያስፈልጋል፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብም ማስረጽ ይገባል፡፡ ለዚህም የማዕከሉ መቋቋም ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል፡፡
የማዕከሉ ዋንኛ ተግባር በዘርፉ ከፍተኛ እውቀትና ልምድ ባላቸው ምሁራን ስልጠና መስጠት ነው፡፡ አስተምህሮው የመንግሥት ተቋማትንና የሲቪክ ማኅበራትን ጨምሮ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች በመጠቀም ይተገበራል፡፡ የማዕከሉ መዋቅር ተሠርቶ ለፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ገብቷል፤ መዋቅሩ ሲፀድቅም የሰው ኃይል በማሟላትና ዕቅድ በማዘጋጀት ወደተግባር እንደሚገባ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ