በኢትዮጵያ ግብርና ላይ ትኩረት ያደረገ የኢንቨስትመንት ትውውቅ በኔዘርላንድ ተካሄደ፡፡

329
በኢትዮጵያ ግብርና ላይ ትኩረት ያደረገ የኢንቨስትመንት ትውውቅ በኔዘርላንድ ተካሄደ፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 21/2013 ዓ.ም (አብመድ) በኔዘርላንድ ሄግ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አዲስ አበባ ከሚገኘው የኔዘርላንድ ኤምባሲ ጋር በመተባበር “ትኩረት ለኢትዮጵያ የግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ” በሚል ርእስ በበይነ መረብ ውይይት አካሂዷል፡፡
በውይይቱም ከ50 በላይ የሚሆኑ የደች ኩባንያዎችና የተለያዩ በዘርፉ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ አድርገዋል፡፡
በኔዘርላንድስ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሚሊዮን ሳሙኤል በአሁኑ ወቅት በተለይም በአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ላይ በርካታ ቁጥር ያላቸው የደች ባለሃብቶች በኢትዮጵያ እየተሳተፉ ነው ብለዋል፡፡
ባለሃብቶች በግብርና ዘርፍ ያለውን እምቅ አቅም በመረዳት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
በግብርናው መስክ ላይ ያለውን አቅምና የገበያ ዕድሎች በመገንዘብ ከኔዘርላንድ ጋር በይበልጥ ለመተሳሰር ውይይቱ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑን ተጠቅሷል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ወንዳለ ሀብታሙ የግል ዘርፉን በግብርና ላይ በስፋት ተሳታፊ ለማድረግ ሚኒስቴሩ ከፍተኛ ማሻሻያ በማድረግ ላይ የሚገኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሃገሪቱ መልማት ከሚችለው መሬት 1/6ኛ ብቻ እየተጠቀመች በመሆኑ ምርታማነትን ለመጨመር የግሉን ዘርፍ በስፋት ማካተት እንደሚገባ በመረዳት ከፖሊሲ ጀምሮ የተለያዩ አሠራሮች እየተሻሻሉ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
ኢንቨሰትመንት ኮሚሽንን በመወከል የተሳተፉት የኢንስትመንት ፕሮሞሽን ባለሙያ ረድኤት ይህዓለም ባቀረቡት ገለጻ ኢትዮጵያን በግብርና ዘርፍ ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ የሚያደርጓት ምቹ ዕድሎች ላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡
በሰሊጥ፣ በወተትና ወተት ተዋጽኦ፣ በእንስሳት መኖ እና በዶሮ እርባታ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት አቅም ያላት መሆኗንና ለዚህ ዘርፍ የተመቻቹ ማበረታቻዎች ላይ ማብራራርያ ሰጥተዋል፡፡
በአዲስ አበባ የኔዘርላንድስ ኤምባሲ የግብርና አማካሪ ሚዌስ ብሮዎር እንዳሉት በአሁኑ ወቅት ከ85 በላይ የሚሆኑ የደች ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ ነው፡፡ ከዚህም 80 በመቶ የሚሆኑት በግብርና ላይ ተሰማሩ መሆናቸውንና ኔዘርላንድስ የኢትዮጵያ የወጪ ምርት ተደራሽ ከሆኑ ሀገራት መካከል በዋናነት ተጠቃሽ ሀገር መሆኗን ገልጸው በኔዘርላንድስ ትኩረት የሚሰጥባቸውን የግብርና መስኮች ላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡
ዋጊኒገን ዩኒቨርሲቲ እና ምርምር ማዕከል የዓለም አቀፍ ትብብር የአፍሪካ አስተዳዳሪ ጄኒ ቫንደርሚሂን እንዳሉት ዩኒቨርስቲያቸው በግብርና ዘርፍ ላይ የሚደረግን ኢንቨስትመንት ለማገዝ የጥናት ተቋሙ ያለውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።
በውይይቱ ላይ በኢትዮጵያ በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሠማሩ የደች ኩባንያዎች ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡
መረጃው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘ ነው፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“የሚያዛልቀን አማራን የምታከብርና አማራም የሚከበርባት ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያን የሚያከብርና ኢትዮጵያም የምትከብርበት አማራ መገንባት ነው” አቶ ተመሥገን ጥሩነህ
Next articleእውነተኛ የፌዴራሊዝም ሥርዓት መተግበር የሚያስችል ማዕከል እያቋቋመ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ፡፡