
“የሚያዛልቀን አማራን የምታከብርና አማራም የሚከበርባት ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያን የሚያከብርና ኢትዮጵያም የምትከብርበት አማራ መገንባት ነው” አቶ ተመሥገን ጥሩነህ
ባሕር ዳር፡ ጥር 21/2013 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር የነበሩት ተመሥገን ጥሩነህ በባሕር ዳር አሸኛኘት ተደርጎላቸዋል። የአሁኑ የብሔራዊና መረጃ ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል ተመሥገን ጥሩነህ በአሸኛነት ዝግጅቱ ላይ ንግግር አድርገዋል።
በንግግራቸው ታሪክ ተቀያያሪ ሁነቶች የጊዜ ቅደም ተከተላቸውን ይዘው ላይመለሱ የሚያልፉበት ሀዲድ ነው ብለዋል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል በርካታ ነገሮች እንደታዩ የተናገሩት አቶ ተመሥገን የትህነግን ኃይል ለመነጠል የፖለቲካ ለውጦች የተደረጉበት፣ ተወዳጅ የትግል አጋሮች የታጡበት፣ በልዩ ልዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ዜጎች በማንነታቸው ዘር ተኮር ጥቃት የተፈፀመበት፣ እጃችንን ዘርግተን የተቀበልናቸው እጃችንን የነከሱበት ሁነቶች ታይዋል ነው ያሉት።
ወደ አማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድርነት ሲመጡ ጊዜው ፈታኝ እንደነበርም አስታውሰዋል አቶ ተመሥገን። ክልሉንና ሀገሪቱን ለማተራመስ ታጋዮቻችንን በሞት ቀምተውናል ነው ያሉት። የሕዝቡን አንገት ሰብረው ራሱን ዝቅ እንዲያደርግ በእጃችን የበላ ተረከዙን አነሳብን፣ በአጎረስናቸው ተነከስን፣ በፈታናቸው ተገደልን ነው ያሉት። ክልሉን ከዚያ ውዥንብር አውጥቶ ወደ ብልፅግና እንዲገሰግስ ለማድረግ ሰላምና ደኅንነት፣ የሕዝቦች መቀራረብና የኢኮኖሚ እድገት ላይ አተኩረው መስራታቸውንም ተናግረዋል።
“ካለፍነው ዘመን ይልቅ የሚመጣው ረጅምና የተሻለ ነው”ብለዋል አቶ ተመስገን።
ወቅቱ እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር በፈተናና እና በተስፋ መካከል መሆኑንም አመላክተዋል። የክልሉ ዋና ፈተና እና ፈታኝ አሁን ላይ አለመኖሩን የተናገሩት አቶ ተመሥገን የፈተናው አለመኖር የክልሉን ሰላምና ብልፅግና ለማረጋገጥ ትልቅ እፎይታ ይሰጣል ነው ያሉት። በሌላ በኩል ከዚህ በኋላ ለሚፈጠረው ችግር እኛው ራሳችን እንጂ ሌላ ማንም ስለማይሆን ደካማና ብርቱው እንዲለይ ያደርጋል ብለዋል።
በክልሉ ሰሜን ምዕራብና ሰሜን ምሥራቅ የነበረው ሕዝብ ለዘመናት የማንነት ጥያቄ ነበረው ያሉት አቶ ተመሥገን ጥያቄው በሕግ አግባብ እንዲፈታ ትህነግ ስለማይፈልግ ሕዝቡን ሲያሰቃይና ጥያቄውን ሲያዳፍን ኖሯልም ነው ያሉት። አሁን የችግሩ ፈጣሪ ሞቷል፣ ከዚህ በኋላ ሕዝባችን በፈለገው መንገድ እንዲተዳደር እድል ተፈጥሮለታልም ብለዋል። አባቶቻችን ያቆሟትንና የተሰዉላትን ሀገር በነፃነትና በአንድነት እንድትኖር ለማድረግ ከባድ ኃላፊነት አለብንም ነው ያሉት።
ትህነግ የዘራው ዘር በአንድ ማዕልት ተገፎ የሚጠፋ ባለመሆኑ ትግል ይጠይቃልም ነው ያሉት።
“የሚያዛልቀን አማራን የምታከብርና አማራም የሚከበርባት ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያን የሚያከብርና ኢትዮጵያም የምትከብርበት አማራ መገንባት ነው” ብለዋል። አንዱ በአንዱ መስዋዕትነት አይገነባም፣ አንዱ ያለ ሌላው አይኖርም፣ ሁሉም በልካቸው መኖር አለባቸውም ነው ያሉት።
ክልሉንና ሀገሪቱን ለኑሮና ለሥራ ምቹ ማድረግና ኢትዮጵያን ጠንካራ ሀገር አድርጎ መገንባት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። ሁሉም ክልሎች አብረው ካላደጉ በአንድ እጅ ሳይሆን በአንድ ጣት ማጨብጨብ ነውም ብለዋል። ወሬውንና መገፋፋቱን በመተው ሀገር የሚለውጥ የተጨበጠ ተግባርና ውጤት ላይ ማተኮር እንደሚገባም አሳስበዋል።
ለትህነግ መደምሰስ መስዋዕትነት የከፈሉ የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ፣ እውነተኛው ፋኖ፣ የአፋር ልዩ ኃይልና ሚሊሻ፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትና የሀገሪቱ ሕዝቦች ምስጋና ይገባቸዋልም ብለዋል።
“በቀያችሁ እንዳትኖሩ ተፈርዶባችሁ፣ በትህነግ ስትሳደዱ፣ ስትታሰሩ፣ ስትገደሉ የነበራችሁ የወልቃይት፣ የጠገዴ፣ የራያ፣ የኮረም ሕዝቦችና የዋልድባ መነኮሳት በተወለዳችሁበት መንደርና በገደማችሁት ገዳም በሰላም፣ በፍቅርና በፀሎት ለመኖር የሚያስችል ደወል ተደውሏልና በማንነታችሁ ኮርታችሁ ለመኖር መብቃታችሁ እንኳን ለዚህ አበቃችሁ” ብለዋል አቶ ተመሥገን። በብዙ ውጣ ውረድ የተገኜውን ድል ጠብቆ ለመዝለቅ አካባቢውን መጠበቅና ለልማት መትጋት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።
“ማንነታችሁን ተነጥቃችሁ ከቆያችሁበት የግዞት ዘመን ወደ ብሩህ ተስፋ የምትሻገሩት በራሳችሁ ትልቅ ተግባርና በመንግሥት ውስን ድጋፍ ብቻ ነው” ብለዋል። ሀገር ማዳንና ለትውልድ ማቆዬትን አስበን ከተንቀሳቀስን ሁሉም ነገር ይታለፋል ነው ያሉት። የአሁኗን ብቻ ሳይሆን የነገዋን ኢትዮጵያን እያሰቡ መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የሀገሪቱ ሕዝቦች በቆዬው እንድነታቸውና አብሮነታቸው እንዲሠሩም ጠይቀዋል። የአማራ ሕዝብ ከትግራይ ሕዝብ ጋር የማይበጠስ ቁርኝት ያለው ሕዝብ መሆኑን የተናገሩት አቶ ተመሥገን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የትግራይ ክልል ወደ መደበኛው እንቅስቃሴ እስኪመለስ ድረስ ድጋፍ ማድረግ አለበትም ብለዋል።
“ከተባበርን ኢትዮጵያውያን ማንም አያሸንፋትም፣ ምክንያቱም እኛ የጀግኖች ልጆች ጀግኖች ስለሆን ነው” ብለዋል። ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚጥሩ ሁሉ የጊዜ ጉዳይ እንጂ እንደሚከስሙም ተናግረዋል። ለሁሉም የተመቸች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ከመልካሙ ሕዝብ ጋር በመሆን የሚቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉም ገልፀዋል።
የአማራ ክልል መሪዎችም በየአቅጣጫው በሚለቀቁ መረጃዎች ሳይወናበዱ በዓላማቸው ፀንተው ለክልሉ የሚመጥን ሥራ እንዲሰሩም ጠይቀዋል። አሁን የሚመሩት ተቋም ስሙ መልካም እንዳልሆነ የተናገሩት አቶ ተመሥገን በፊት ስሙ ሲጠራ የሚያስፈራ፣ አሁን ማንም የሚሰድበው ተቋም ነው፣ እኔ ያቀድኩት የተሻለ ለማድረግ ነውም ብለዋል። መጥፎ ሥራ የሚሠሩ መሪዎችን ጨምሮ ሌሎች አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:-ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ