
“የሕዝብ ልጆች ስለሆን በሙያችን ከፊት ተሰልፈናል እንጂ ሊደነቅ የሚገባው ከጎናችን ያልተለየው የሰሜን ወሎም ሆነ የአማራ ሕዝብ ነው” የአማራ ልዩ ኀይል የመቅደላ አምባ ብርጌድ ምክትል አዛዥ
ባሕር ዳር፡ ጥር 19/2013 ዓ.ም (አብመድ) የወልድያ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ መምህራን፣ ሠራተኞችና ተማሪዎች ለአማራ ልዩ ኀይልና ሚሊሻ ከ96 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ አሰባስበዋል፡፡ በተሰበሰበው ገንዘብም የፍየል ሙክቶች ገዝተው በወልድያና አላማጣ ለሚገኙ የአማራ ልዩ ኀይል አባላት ለግሰዋል፡፡ የኮሌጁ ዲን ሰለሞን አየሁ ድጋፉን ሲያስረክቡ እንደተናገሩት የኮሌጁ ማኅበረሰብ በጦርነቱ ወቅት በወልድያ ሆስፒታል ይታከሙ ለነበሩ የሠራዊት አባላት የአልባሳትና የለስላሳ መጠጦች ድጋፍ እንዳደረገ አስታውሰዋል፡፡
ሀገር ወደ ተረጋጋ ሁኔታ እስክትገባ ድረስ ሰራዊቱ የህግ ማስከበርና የሠላም ማስፈን ሥራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡
የኮሌጁ የድጋፍ ገንዘብ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለ ደረሱ “እኛ በተመቻቸ ቤት በዓል እየዋልን የኛ ሰራዊት ግን ባልተመቻቸ ሁኔታ ስለሆነ ያለው ቢያንስም ለበዓል መዋያ ለማበርከት መጥተናል” ብለዋል፡፡
የአማራ ልዩ ኀይል የመቅደላ አምባ ብርጌድ ምክትል አዛዥ ኮማንደር ቀኘ ገብረመስቀል ድጋፉን በአላማጣ ከአባሎቻቸው ጋር ሲረከቡ “እኛ የሕዝብ ልጆች ስለሆን በሙያችን ከፊት ተሰልፈናል እንጂ ሊደነቅ የሚገባው ከጎናችን ያልተለየው የሰሜን ወሎም ሆነ የአማራ ሕዝብ ነው” በማለት አመስግነዋል፡፡
ድሉ የሕዝቡ ነው ያሉት ኮማንደር ቀኘ፤ ከአያቶቻችንና ከአባቶቻችን የወረስነውን የመተባበርና የመዝመት ልማዳችን ዛሬም በመድገም አንድነታችን ጠብቀን ልንቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡
ድጋፉ የተሰበሰበው ከኮሌጁ መምህራን፣ ሠራተኞችና ተማሪዎች እንዲሁም በኮሌጁ ስር ካሉ የክዘናና የአጸደ ህጻናት ትምህርት ቤት መምህራንና ሠራተኞች እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡
ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ- ከወልድያ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ