
የፌደሬሽን ምክር ቤት ለክልሎች ለሚሰጠው የድጎማ በጀትን ግልጽ አሠራር ለመዘርጋት ጥናት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 18/2013 ዓ.ም (አብመድ) የፌደሬሽን ምክር ቤት
ተግባራዊ ከተደረገው ጥቅል ዓላማ ካለው የድጎማ በጀት አሠራር በተጨማሪ የተመጣጠነ እድገት ለማምጣት ታሳቢ ያደረገ ልዩ ዓላማ ያለው የድጎማ ስርዓት ለመበጀት እየሠራ መሆኑን ገልጿል።
ምክር ቤቱ እያከናወነ ያለውን የሪፎርም ተግባር ከፌደራል፣ የክልልና ከተማ አስተዳደሮች ምክር ቤቶች ጋር ተወያይቷል።
የሪፎርሙ አስፈላጊነት፣ ይዘት፣ አሁን ያለበት ደረጃና የሚጠበቁ ውጤቶች አንዲሁም ሌሎች በሪፎርሙ የተካተቱ ጉዳዮች ላይ ለውይይት መነሻ ቀርቧል።
ቀደም ሲል ለክልሎች የሚሰጠው የድጎማ በጀት ግልጽ መስፈርት እንዳልነበረውና ከስምንት ጊዜ በላይ ማሻሻያ እንደተደረገበትም ተነስቷል። ሆኖም የክልሎችን እድገት ለማመጣጠን የሚሰጠው በጀት ለምን ዓላማ እንደሚውል የተዘረጋ ግልጽ አሠራር እንዳልነበረ ነው የተገለጸው።
የፌደሬሽን ምክር ቤት እያደረገ ባለው የሪፎርም ሥራ ትኩረት ከሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ ለድጎማ በጀት ግልጽ አሠራር መዘርጋት መሆኑ ነው የተጠቀሰው።
የውይይቱ ተሳተፊዎችም በሥራ ላይ ያለው የድጎማ በጀት የአሠራርና፣ የመረጃና የተጠያቂነት ክፍተት በስፋት እንደሚስተዋልበት አንስተዋል።
የሚበጀተው በጀት ቁጥጥርና ክትትል የሚደረግበት አሠራር እንዳልነበር ጠቅሰው ቀጣይ መታየት ያለበት ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል።
የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ በሰጡት ማብራሪያ አሁን በሥራ ላይ ያለው የድጎማ በጀት መሰረት የሚያደርገው የክልሎችን የገቢ አቅምና በስምንት ዋና ዋና ዘርፎች የክልሎች የወጪ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልጸዋል።
እነዚህ መስፈርቶች የተቀመጡበት የመረጃ ጥራትና ግልጽነት የሚጎድለው እንደሆነ ያነሱት አፈ ጉባኤው እስካሁን ሲዘጋጁ የነበሩ ቀመሮች ያሉባቸው መሰረታዊ ክፍተቶች በጥናቱ ይታያሉ ብለዋል።
የፌደራል መንግስት ለክልሎች የሚሰጠው የድጎማ በጀት ለተፈለገው ዓላማ መዋሉን ቁጥጥር የሚደረግበት አሠራር ይዘረጋልም ነው ያሉት።
አሁን ተግባራዊ ከተደረገው ጥቅል ዓላማ ካለው ድጎማ በተጨማሪ እያንዳንዱ ክልል ያለበትን ክፍተት በማየት የተመጣጠነ እድገት ለማምጣት ታሳቢ ያደረገ ልዩ ዓላማ ያለው የድጎማ ስርዓት ለመበጀት እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል።
የፌደሬሽን ምክር ቤት እያካሄደ ያለው የሪፎርም ጥናት በሰው ኃይል፣ በአደረጃጀትና በሌሎችም ራሱን በማጠናከር የተሰጠውን ዓላማ በብቃት ለመፈጸም ያለመ ነው፤ በቀጣዮቹ ወራት ይጠናቀቃልም ተብሏል።
ኢዜአ እንደዘገበው፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ