
“ከታኅሣስ ወር ጀምሮ 800 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ዩኒየኖችና ኅብረት ሥራ ማኅበራት ለማጓጓዝ ችለናል” የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ
ባሕር ዳር፡ ጥር 18/2013 ዓ.ም (አብመድ) የግብርና ሚኒስቴር ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ፣ ከትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭ አካላት፣ ከኅብረት ሥራ ኤጀንሲዎች፣ ከዩኒየኖችና ከዞን ከግብርና የኅብረት ሥራ ጽሕፈት ቤት ኀላፊዎች ጋር ለ2013/2014 የምርት ዘመን የሚውሉ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች በወቅቱ በሚደርሱበት ሁኔታ ላይ በባሕር ዳር ምክክር አድርገዋል።
የ2013/14 የምርት ዘመንን ለማሻሻል በየደረጃዉ የሚገኙትን ባለ ድርሻ አካላት የማሰልጠን፣ ውይይትና የንቅናቄ ሥራ መሥራት፣ የማከማቻ ቦታዎችን የማዘጋጀትና ሌሎች ተግባራትን ሲፈፅሙ መቆየታቸዉን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ መለስ መኮንን (ዶክተር) ተናግረዋል።
በተያዘው ዓመት ከ7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ለምነትን የሚያሻሽል ማዳበሪያ ለማስገባት ሥራቸውን ቀድመው ማከናወን እንደጀመሩ ነው ዶክተር መለስ የጠቆሙት።
“የአፈር ማዳበሪያ ግብዓት ስርጭት ከጥር በፊት ተጀምሮ አያውቅም ነበር። በዘንድሮዉ ዓመት ግን ከታኅሣስ ወር ጀምሮ 800 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ዩኒየኖችና ኅብረት ሥራ ማኅበራት ለማጓጓዝ ችለናል” ያሉት ኀላፊው በቀጣይ በመጓጓዝ ሂደቱ ሊገጥም የሚችለውን ችግር ዞኖችና ወረዳዎች የማስተካከል ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች እንዲደርስ በማድረግ በኩል ሚናቸውን ከሚወጡ ባለድርሻ አካላት አንዱ የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማስፋፊያ ኤጀንሲ ይጠቀሳል። ኤጀንሲው 23 ማከማቻ ያላቸው ዩኒየኖች እንዲሁም 1 ሺህ 555 መሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራት የአፈር ማዳበሪያን በወቅቱ ለአርሶ አደሮች እንዲያደርሱ ለማድረግ እንደሚሠራ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ኀይለልዑል ተስፋ አስረድተዋል።
በአማራ ክልል በ2013/14 የምርት ዘመን ከ8 ሚሊዮን በላይ የአፈር ማዳበሪያ እንደሚሰራጭ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። ዘንድሮም በፍጥነት ለአርሶአደሮች እንዲደርስ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ተካሂዷል ብለዋል፡፡
አቶ ሲሳይ ታረቀኝ በጥቁር ዓባይ ትራንስፖርት ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የማርኬቲንግ መምሪያ ሥራ አስኪያጅ ናቸው። የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ሊዘገይ የሚችለው በመንገድ ምቹ አለመሆን፣ የትራንስፖርት አቅራቢ ድርጅቶች በገቡት ውል መሠረት አገልግሎት አለመስጠት እና የማከማቻ ቦታዎች የቆየ የአፈር ማዳበሪያን ይዘው መገኘት ምክንያት እንደሆነ ጠቁመዋል።
በተያዘው የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ ለአርሶ አደሮች እንዲደርስ ይሠራል ነው ያሉት::
ዘጋቢ:- ብሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ