
የደቡብ ዕዝ ለወልድያ ከተማ ነዋሪዎች እውቅና ሰጠ።
ባሕር ዳር፡ ጥር 15/2013 ዓ.ም (አብመድ) በኢፌዲሪ መከላከያ ሚኒስቴር የደቡብ ዕዝ ደረጃ 3 ሆስፒታል አባላትና ሙያተኞች ለወልድያ ከተማ ነዋሪዎች የእውቅናና የምስጋና ፕሮግራም አቅርቧል።
መንግሥት በወሠደው ሕግ በማስከበር ዘመቻ ወቅት ጉዳት የደረሰባቸውን የደቡብ ዕዝ የሠራዊት አባላትን በመንከባከብ የወልድያ ከተማ ነዋሪዎች ላሳዩት ተግባር የእውቅና መርኃ ግብሩ መካሄዱ ተገልጿል፡፡
የደቡብ ዕዝ ደረጃ ሦስት ወታደራዊ ሆስፒታል አዛዥ ኮሎኔል በቀለ ባሳ የወልድያ ከተማና አካባቢው ማኅበረሰብ መንግሥት ባደረገው ሕግ የማስከበር ዘመቻ ከሠራዊቱ ጎን በመሆን ያደረጋችሁትን አኩሪና ዘመን ተሻጋሪ ገድል ሁሌም የምንዘክረው ነው ብለዋል።
“የወልድያ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች በአኩሪው ሁለንተናዊ ገድላችሁ ዘወትር እናወሳችኋለን” ያሉት ደግሞ ኮሎኔል ፋንታሁን ተፈራ የራያ ግንባር ህክምና አስተባባሪና የደቡብ ዕዝ ጤና መምሪያ ኃላፊ ናቸው።
ኮሎኔል ፋንታሁን ሠራዊቱ በወሰደው ሕግ የማስከበር ዘመቻ ወቅት የወልድያ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ጉዳት ለደረሰባቸው የሠራዊት አባላት ስንቅ ከማቅረብ ጀምሮ በጉልበትና የማይነጥፍ ሞራል መለገሳቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
“በጀግናው ሠራዊታችን እና በመላው ህዝባችን ገድል የሀገራችን ሠላም ተረጋግጧል፤ የወልድያ ህዝብ ያደረገው ሰናይ ተግባር ወደፊት ታሪክም በኩራት የሚያነሳው ነው፤ ክብርና አድናቆት አለን” ብለዋል ኮሎኔል ፋንታሁን።
በምስጋናና የእውቅና የመስጠት መርኃ ግብር ላይ የደቡብ ዕዝ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የሠራዊት አባላት፣ የሰሜን ወሎ ዞን የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የፀጥታ አካላት፣ የወልዲያ ከተማ ነዋሪዎች እና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል፡፡ መረጃው ከሀገር መከላከያ ሠራዊት የማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘ ነው፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ