
“ዘመቻው ቢያልቅም ዘመቻው የፈጠራቸው ዕድሎችም፤ ዘመቻው ያስከተላቸው ጫናዎችም አላለቁም” ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት
ባሕር ዳር፡ ጥር 15/2013 ዓ.ም (አብመድ) በትግራይ ክልል የተከናወነው ህግን የማስከበር ዘመቻው ቢያልቅም፤ የፈጠራቸው ዕድሎችም ሆኑ ያስከተላቸው ጫናዎች እንዳላለቁ ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ተናገሩ፡፡
ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ይህንን ያሉት በህግ ማስከበር ዘመቻ ወቅት ግዳጃቸውን ለመወጣት የሚዲያውን ሥራ ለመስራት የተላኩ ልዑካን ትላንት እውቅና በተሰጠበት መድረክ ላይ ነው፡፡
ዘመቻው በአንድ በኩል መድኃኒትነት ያለውና አገሪቱን ከብዙ ቀውስ ያዳነ መሆኑን ገልጸው፤ በሌላ በኩል ደግሞ የተካሄደው ጦርነት ስለሆነ ያስከተለው ጫናም እንዳለ በምሳሌ አስደግፈው ተናግረዋል፡፡
“አንድ ሰው ሆስፒታል ገብቶ ለጤናው ሲባል ኦፕሬሽን ቢደረግ፤ በአንድ በኩል የሚያመው ነገር ስለወጣለት ይሄ ሰውዬ ድኗል ደስ ይለዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኦፕሬሽን ሲደረግ የተቀደደው ሆዱ ላይ ደግሞ የሚቀር ነገር አለ፡፡ በዚህ ደግሞ የተወሰነ ጊዜ ያመዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ሰው ‘ምነው እዛ ውስጥ ገብቼ ኦፕሬሽን ባልተደረግኩ’ አይልም፡፡
“ተስፋ የሚያደርገው መዳኑን ስለሆነ የተወሰነ ጊዜ ህመሙን ይሸከመዋል፡፡ ይታገሰዋልም፡፡ ሰውም ደግሞ ‘ኧረ እንኳን ተሻለህ ይህንን ቁስልህን የውሻ ቁስል ያድርግልህ’ ይለዋል እንጂ አፕሬሽን መሆን አልነበረብህም አይለውም፡፡ አሁንም በህግ ማስከበር ዘምቻው የተከናወነው ነገር እንደዛው ነው፡፡” ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ልክ ኦፕሬሽን እንደተደረገው ሰውዬ ዘመቻው ያስከተለው ጫና እንደለ ጠቁመው፤ ችግሩን በመቀነስ ጥቅሙን በመጨመር የኢትዮጵያን ህብረ ብሄራዊ አንድነት በማጽናት መቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሚዲያው ሚና ሰፊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
“በዘመቻው ላይ እንዳሳየነው ህብረት፣ አንድነትና መተጋገዝ ለሌሎች ነገሮችም እንዲሁ ኢትዮጵያን ወደምንፈልጋትና ህዝቡ ወደሚጠይቀው ደረጃ እናደርሳለን” ማለታቸውን የዘገበው ኢትዮ ፕረስ ነው፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ