ፍርድ ቤቱ ጃዋር መሐመድን ጨምሮ የ18 ተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ።

349
ፍርድ ቤቱ ጃዋር መሐመድን ጨምሮ የ18 ተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ።
ባሕር ዳር፡ ጥር 14/2013 ዓ.ም (አብመድ) የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የፀረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት ጃዋር መሐመድን ጨምሮ 18 የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ጥር 04 ቀን 2013 ዓ.ም ላይ በነበረው ችሎት እንዲያሻሽላቸው ከታዘዘው የተወሰኑትን አሻሽሎ አቅርቧል።
ነገር ግን ዐቃቤ ሕግ ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ የፀረ ሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ችሎት ማመልከቻ አቅርቧል። የማመልከቻው ይዘት በእነ ጃዋር የክስ መዝገብ አምስት ክሶች በተለይም ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ይዞ መገኘት ጋር በተያያዘ አዋጁን ጠቅሶ ዋናው ክስ ላይ የጠቀሰውን የክስ ጭብጥ ፍርድ ቤቱ እንዲያሻሽል ትእዛዝ ቢሰጥም ማሻሻል እንደማይችል የተለያዩ ምክንያቶች ጠቅሶ ማመልከቻ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል።
ችሎቱም የተወሰነ ጊዜ ወስዶ የዐቃቤ ሕግን ማመልከቻ መርምሯል። በመሆኑም ከጦር መሣሪያ አዋጅ ጋር በተያያዘ ፍርድ ቤቱ ቀደም ሲል የሰጠው ትእዛዝ አሳማኝ መሆኑን ጠቅሶ ዐቃቤ ሕግ ከጦር መሣሪያ ጋር ተያየዝ በተከሳሾች ላይ ያቀረበውን ክስ የማያሻሽል መሆኑን በመገንዘብ እንዲቋረጥ ትእዛዝ ሰጥቷል።
ይህንንም ተከትሎ ፍርድ ቤቱ የእምነት ክህደት ቃል እንዲሰጡ ተከሳሾችን ጠይቋል፤ ነገር ግን የተከሳሽ ጠበቆች “ተሻሽሏል የተባለውን ክስ በአግባቡ ለመረዳት ጊዜ ስለሚያስፈልግ እና ከደንበኞች ጋር ለመመካከር ስለሚያስፈልግ አሁን ባለንበት ሁኔታ የእምነት ክህደት ቃል ለመስጠት ያስቸግራል፤ ስለዚህ አጭር ቀጠሮ ይሰጠን” በማለት አመልክተዋል።
ተከሳሾችም በዛሬው ቀጠሮ የእምነት ክህደት ቃል ለመስጠት ዝግጁ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።
ይህንን ግምት ውስጥ ያስገባው ችሎቱ ተከሳሾች ጠበቆች ከጠቀሱት ወሳኝ በሚባለው የእምነት ክህደት ቃል መስጠት ጋር በተያያዘ በቂ ዝግጅት አድርገው እንዲመጡ ለመጪው ረቡዕ ጥር 19 ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን የኢቢሲ ዘገባ አመልክቷልተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበጎንደር ከተማ አስተዳደር የትምህርት ተቋማትን ደረጃ ወደ 50 በመቶ ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑን ከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡
Next articleወጣቶች በሀገር ግንባታ ላይ የድረሻቸውን እንዲወጡ የሚመክር መድረክ በእንጂባራ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡