
ከተሞችን በእቅድና በቅንጅት መምራት እንደሚገባ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ ተናገሩ፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 14/2013 ዓ.ም (አብመድ) በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የተዘጋጀው የክልሎች ስፓሻል እቅድ ጥናት አተገባበር በጎንደር ውይይት እየተደረገበት ነው፡፡ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ፈንታ ደጀን እየጨመረ የመጣውን የከተሜነት ፍላጎትን በአግባቡ ለማስተዳደር፤ የተሞችን ሃብት አውቆ ለመምራት እና ከተሞች የጠጣጣመና የተቀናጀ እድገት እንዲኖራቸው እቅዱ ወሳኝ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ አሁን ያለው የከተሞች ችግር እቅድ ያለመኖር መሆኑን ገልጸው ከተሞችን በእቅድና በቅንጅት መምራት ከተቻለ እየገጠማቸው ያለውን ቀውስ መቀነስ ይቻላል ብለዋል፡፡
ከተሞች ከገጠር አካባቢዎች እና ከአጎራባች ከተሞች ጋር ያላቸውን መስተጋብር በማስተካከልም የከተሞችን እድገት ጤናማ ማድረግ እንደሚገባ ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ አሳስበዋል፡፡
የክልሎች ስፓሻል እቅድ በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የሚዘጋጅ ሲሆን፤ የክልል ከተሞች ያላቸውን ሃብት የሚያመላክት እና በአግባቡ ማስተዳደር የሚያስችል ነው፡፡
እቅዱ ከተሞች ካላቸው መሪ እቅድ ጋርም አቀናጅቶ ለመምራት የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡ በውይይቱ የአማራ፣ የአፋርና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኀላፊች እንዲሁም ከንቲባዎች እየተሳተፉ ነው፡፡
ዘጋቢ፡- አብርሃም አዳሙ – ከጎንደር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ