
ኑሯቸውን በአሜሪካ ያደረጉ የአማራ ክልል ተወላጆች ለመተከል ተፈናቃዮች ድጋፍ አደረጉ፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 14/2013 ዓ.ም (አብመድ) ኑሯቸውን በአሜሪካ ሀገር ያደረጉ የአማራ ክልል ተወላጆች ከመተከል ዞን ተፈናቅለው በቻግኒ ከተማ አቅራቢያ ለተጠለሉ ዜጎች ከ280 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የዕለት ደራሽ ድጋፍ አደረጉ፡፡
ከተደረጉ ድጋፎች ውስጥም ከ 35 ኩንታል በላይ በርበሬና ሽሮ እንዲሁም አልባሳት ይገኙበታል፡፡ አቶ ሽባባው የኔአባት ከለጋሾቹ የተሰበሰበውን ድጋፍ በተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ በአካል ተገኝተው አስረክበዋል፡፡
በድጋፍ ርክክብ ወቅትም ብዙኀን መገናኛ የተፈናቃዮችን ሰቆቃ በችግሩ ስፋት ልክ አጉልተው በማሳየት ለጋሾች እንዲደርሱላቸው ማድረግና ችግሩ ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኝ ግፊት ማድረግ አለባቸው ብለዋል፡፡ ችግሩ ዘላቂ መፍትሔ እስኪያገኝ ድረስ ለጋሾችን በማስተባበር ለተፈናቃዮች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አቶ ሽባባው ገልፀዋል፡፡
ድጋፉን የተረከቡት በቻግኒ ከተማ አስተዳደር በጊዜዊነት የተቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ አቶ ጀምበሩ ደሴ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ የሚደርሰውን ድጋፍ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ በፍጥነት እንዲዳረስ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ጀምበሩ ገልፀዋል፡፡
ተፈናቃዮች በበኩላቸው መንግሥት የአካባቢውን ሠላም በፍጥነት በማረጋገጥ ወደ መደበኛ ህይወታቸው እንዲመልሳቸው ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ሳሙኤል አማረ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ