
በአበርገሌ ወረዳ በቢዛን ወንዝ ላይ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የድልድይ ግንባታ ተጀመረ፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 13/2013 ዓ.ም (አብመድ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አበርገሌ ወረዳ ነይረ አቑ ከተማን ከፃላሪ ቀበሌ የሚያገናኝ ሰባት ነጥብ ሰባት ኪሎ ሜትር መንገድ በ2009 ዓ.ም በገጠር መንገድ ተደራሽነት ፕሮግራም (ዩራፕ) ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ተገንብቶ ነበር፡፡
የመንገድ ሥራው በቢዛን ወንዝ ላይ የድልድይ ግንባታን ያላካተተ በመሆኑ የአካባቢውን እንቅስቃሴ አስቸጋሪ አድርጎት ቆይቷል፤ በተለይ በክረምት ወቅት አምቡላንስን ጨምሮ የትራንስፖርት እና የጭነት ተሸከርካሪዎችን መጠቀም እንደማይችሉ የ012 ቀበሌ ነዋሪዎች አቶ በለጠ ወልደዮሀንስ እና መርጌታ ወልደገብርኤል ታደለ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል በ2013 በጀት ዓመት የከፍተኛ ድልድይ ግንባታ ሥራ ከያዛቸው ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የቢዛን ወንዝ ድልድይ 24 ሜትር ርዝመት ግንባታ የማስጀመር ፕሮግራም ነበር። የድልድይ ግንባታ ሥራውም ተጀምሯል፡፡ ድልድዩ ከክልሉ መንግሥት በተበጀተ 10 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር እንደሚገነባ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አቶ በሪሁን ኪዳነማሪያም ገልጸዋል፡፡ በአራት ወራት ውስጥ ተጠናቆ አገልግሎት ይሰጣልም ብለዋል።
የድልድዩ ግንባታ ሲጠናቀቅ የኅብረተሰቡን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጎላ አስተዋፅኦ እንዳለውም በግንባታ ማስጀመር ፕሮግራሙ ላይ ተጠቅሷል። በፕሮግራሙ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ የወረዳ የሥራ ኀላፊዎች እና የአከባቢው ማኅበረስብ ተገኝተዋል።
ዘጋቢ:- ፀጋዬ አይናለም-ከአበርገሌ ወረዳ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ