
የግዮንን በዓል ለሦስተኛ ጊዜ በደመቀ ሁኔታ ለማክበር የሰከላ ወረዳ ዝግጅቷን አጠናቃለች፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 12/2013 ዓ.ም (አብመድ) የግዮንን በዓል ለሦስተኛ ጊዜ በደማቅ ሁኔታ በማክበር ለሀገር ውስጥና ለውጭ ጎብኝዎች ለማስተዋወቅ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን የሰከላ ወረዳ አስታውቋል፡፡
ሰከላ የታላቁ የዓባይ ወንዝ መነሻና የአቡነ ዘርዓብሩክ ፀበል መገኛ ናት፡፡ የአካባቢውን የመስህብ ሀብት በሀገር አቀፍና በዓለም አቀፍ መድረክ በማስተዋወቅ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠሩ መሆኑን የሰከላ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ በእውቀት ተሾመ ነግረውናል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ዋና አስተዳዳሪው ገልፀዋል፡፡ ወጣቶችን በማደራጀት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል የሚያቀርቡበት ሁኔታም ተመቻችቷል ብለዋል፡፡
በዓሉን ያለምንም የጸጥታ ችግር ለማክበር ፖሊስ፣ ሚሊሻና የጸጥታ መዋቅሩ ተቀናጅቶ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ በዓሉ ነገ ጥር 13/2013 ዓ.ም ለሦስተኛ ጊዜ በደመቀ ሁኔታ ይከበራል ያሉት አስተዳዳሪው በዕለቱ ለሚፈጸም ወንጀል አስቸኳይ ዳኝነት የሚሰጥበት ጊዜያዊ የችሎት ቦታም መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡
በበዓሉ የወረዳው የእደ ጥበብ ምርቶች ለገበያ ይቀርባሉ፤ኤግዚቢሽን ይካሄዳል፤ ሩጫ፣ የፈረስ ጉግስ፣ ስፖርታዊ ውድድሮች የበዓሉ ድምቀት እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡
ወረዳዋ የዓባይ ወንዝ መነሻ የግሼ ተራራ፣ የፋሲል ግንብ ( አጼ ፋሲል ጎንደር ከመግባታቸው በፊት የገነቡት)፣ የጉደራ ሐይቅ፣ የአላዛር ዋሻ እና ሌሎች የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ይገኛሉ፡፡ እነዚህን እና ሌሎችን ዕምቅ የመስህብ ሀብቶች ለማስተዋወቅ በዓሉ መከበሩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል፡፡
አቶ በእውቀት እንዳሉት በየዓመቱ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎች ወረዳዋን ይጎበኛሉ፡፡ ይህን በማጠናከር ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ከፍ በማድረግ የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ ነው፡፡
በዓሉ የዓባይ ወንዝን መነሻ ለማስተዋወቅና አካባቢውን ለማልማት ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል አቶ በእውቀት፡፡ የዓባይ ወንዝ መነሻ የሆነውን ቦታ መንከባከብና የህዳሴው ግድብ የታለመለትን ዓላማ እንዲያበረክት የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል ዋና አስተዳዳሪው፡፡
የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች መዋዕለ ነዋያቸውን በሰከላ ወረዳ ላይ በማዋል ራሳቸውን ብሎም ሌሎችን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ አቶ በእውቀት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ