”ምዕመኑ የጥምቀት በዓል እሴትና ባህልን ልክ እንደ አይኑ ብሌን ሊጠብቀው ይገባል” የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ

263

”ምዕመኑ የጥምቀት በዓል እሴትና ባህልን ልክ እንደ አይኑ ብሌን ሊጠብቀው ይገባል” የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ
ባሕር ዳር፡ ጥር 11/2013 ዓ.ም (አብመድ) ምዕመኑ የጥምቀት በዓል እሴትና ባህልን ልክ እንደ አይኑ ብሌን ሊጠብቀው ይገባል ሲሉ በኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ጅቡቲ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል ገለጹ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ የጥምቀት በዓል ዛሬ በደማቅ ሥነ ሥርዓት ተከብሯል።
በአዲስ አበባ ጃንሜዳ በተካሄደው የበዓሉ ሥነ ሥርዓት ላይ የታደሙትን ብፁዕ አቡነ ዳንኤል እንደተናገሩት በኢትዮጵያና በግሪክ ያለው የጥምቀት በዓል አከባበር ተመሳሳይ እንደሆነና በሁለቱም ሀገሮች ሃይማኖታዊ ሥርዓት ውኃው ተባርኮ ሕዝቡ ይጠመቃል፡፡ ጥምቀቱ የዮርዳኖስ ወንዝና የኢየሱስ ክርስቶስ በረከት የሚገኝበት መሆኑን አመልክተዋል።
በኢትዮጵያም የጥምቀት በዓል አከባበር በጣም ደማቅ መሆኑንና ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የበዓሉን አከባበር ለመታደምና ለመመልከት እንደሚሹ ገልጸዋል።
“በዓሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በታሪክና በሃይማኖት ያላትን ሀብት የሚያሳይ ነው” ብለዋል።
“ምዕመኑ የጥምቀት በዓል እሴትና ባህልን ልክ እንደ አይኑ ብሌን ሊጠብቀው ይገባል” ያሉት ብፁዕ አቡነ ዳንኤል፤ በተለይም ወጣቱ በዓሉ ይዘቱን ሳይለቅ ዘመናትን የማሻገር ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በኢትዮጵያና በግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያናት ለክፍለ ዘመናት የዘለቀውን ትስስር ይበልጥ ለማጎልበትና የሀገራቱን ህዝቦች ግንኙነት ለማጠናከር ቤተክርስትያናቸው እንደምትሠራ ጠቁመዋል። ኢዜአ እንደዘገበው፡፡

Previous article‹‹ወደላይ፣ ልቤን ሰድደኩት እንዲያይ››
Next article“የኢትዮጵያውያን ባሕል ያልተበረዘ በመሆኑ፣ ቀሪው ዓለም ሊማርበት ይገባል”