
በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በዓሉን በዮርዳኖስ ወንዝ በድምቀት አክብራለች።
ባሕር ዳር፡ ጥር 11/2013 ዓ.ም (አብመድ) በዛሬው ዕለት በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ገዳማት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንባቆም እንዲሁም የገዳሙ መነኮሳት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀበት ቦታ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ወርደው በዓሉን አክብረዋል።
በዮርዳኖስ ወንዝ የሚከበረው በዓል ለሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ተራ የተሰጠ ሲሆን፣ ዛሬ የግሪክ ኦርቶዶክስና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ነገ የሶሪያና የግብጽ፣ በቀጣይ የአርመን፣ የሩሲያና ሌሎችም ያከብራሉ።
በዚህ ዓመት የኮሮናወረርሽኝን ለመከላከል በወጣው መመሪያ መሠረት የእንቅስቃሴ ገደብ ስለተጣለ ለመግባት የተፈቀደው ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ በመሆኑ ብዙ ምዕመናን መሄድ አልቻሉም።
የዕለቱ ክብረ በዓል በፀሎት የተጀመረው በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ ባለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ገዳም ነው። ይህ ቦታ ምስጢረ ሥላሴ የተገለጠበት ስለሆነ፣ የተሠራው ገዳም የቅድስት ሥላሴ ታቦት ያለበት መሆኑ ታውቋል።
ይህ ገዳም ለበርካታ ዓመታት ተዘግቶ የኖረ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተከፈተ መሆኑን አባቶች ገልጸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑን እንደገና ለመገንባትም ፈቃድ ተሰጥቷል።
ብፁዕ አቡነ እንባቆም በገዳሙ መግቢያ ላይ ፀሎት አድርሰው ቡራኬ ሰጥተዋል። በመቀጠልም በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ ኪዳን በማድረስና ወንጌል በማንበብ መረሃ ግበሩ ተጠናቋል፡፡
በግሩም ቀለመወርቅ
ምስል- ከድረ ገጽ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ