
ዳያስፖራው ተሳትፎ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል የሚያስችል ፕሮጀክት ሊተገበር ነው፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 09/2013 ዓ.ም (አብመድ) በዳያስፖራው ተሳትፎ ከደረጃ በታች የሆኑ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል የሚያስችል ፕሮጀክት ሊተገበር መሆኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ።
ኤጀንሲው የዳያስፖራውን የበጎ አድራጎት ተሳትፎ ለማሳደግ በሚያስችሉ ፕሮጀክቶች ቀረፃ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሲያካሂድ የቆየው አውደጥናት አጠናቋል።
በአውደጥናቱ ከደረጃ በታች ሆነው ትምህርት እየተሰጠባቸው ያሉ የዳስ ትምህርት ቤቶችን የሚያሻሽል ፕሮጀክት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለመቅረፅ ከመግባባት ላይ ተደርሷል።
የፕሮጀክት ቀረፃውን የልማት ማኅበራት፣ የትምህርት ቢሮዎችና የዳያስፖራ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቶች በጋራ በመሆን የሚያዘጋጁት ይሆናል።
በፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ በተለያየ የገጠር አካባቢ 40 ያህል ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል እቅድ መያዙ ተገልጿል።
የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሀመድ እንድሪስ እንዳሉት ዳያስፖራው በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ ከ67 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የበጎ አድራጎት ስራዎችን አከናውኗል።
ዳያስፖራው እገዛ ከሚያደርግባቸው ዘርፎች ውስጥ የትምህርት ልማት አንዱ መሆኑን ገልፀው፤ ዘርፉን ለማገዝ የታሰቡት ፕሮጀክቶች ውጤታማ እንዲሆኑ ከባለድርሻ ተቋማት ጋር በቅንጅት እንደሚሠራ ተናግረዋል።
የአውደጥናቱ ተሳታፊዎች ዳያስፖራው በተለይ በትምህርትና እውቀት ሽግግር ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ እንዲያሳድግ ጠይቀዋል።
ለትምህርት ዘርፍ እንደመጀመሪያ ዙር የዳያስፖራ በጎ አድራጎት ተሳትፎ ማሳደጊያ ፕሮጀክት ቅድሚያ መሰጠቱን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ዳያስፖራው በሌሎች የልማት ሥራዎች ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ ሳይገደብ ፕሮጀክቱ እንደሚተገበርም ነው የገለጹት።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ