
“የህዝቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ መንግሥት ሰፊ ጥረት እያደረገ ነው” ርእሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር
ባሕር ዳር፡ ጥር 07/2013 ዓ.ም (አብመድ) ከ178 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገበት የኮምቦልቻ ጠቅላላ ሆስፒታል ዛሬ ተመርቋል።
የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ የክልልና የፌዴራል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተመርቋል።
የኢንቨስትመንት ማዕከል የሆነችውን ኮምቦልቻ ከተማን ጨምሮ በዞኑ ለሚገኙ ተገልጋዮች ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ሆስፒታሉ እንደሚያግዝ ተገልጿል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ የኮምቦልቻ ሕዝብ በግንባታው መጓተት ላሳየው ትእግስትና ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው የኮምቦልቻ ጠቅላላ ሆስፒታል የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጥ አስፈላጊ የህክምና ቁሳቁሶች ይሞሉለታል ብለዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር በደቡብ ወሎ ዞን እየተከናወኑ ባሉ የልማት ተግባራት የሕዝቡ ድጋፍ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
“የሕዝቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ መንግሥት ሰፊ ጥረት እያደረገ ነው” ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የኮምቦልቻ ጠቅላላ ሆስፒታል በክልሉ ካሉት ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ከሚያስተናግዱ ሆስፒታሎች ጋር የሚጣጣም ግብዓት እንዲሟላለት ከፌዴራል መንግሥት ጋር በቅንጅት እንሠራለን ብለዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ወጭ የተደረገባቸው የልማት ፕሮጀክቶች በክልልና የፌዴራል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተመርቀዋል።
ዘጋቢ፡- ስማቸው እሸቴ – ከኮምቦልቻ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ