የእገታ ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡

302
የእገታ ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 07/2013 ዓ.ም (አብመድ) በጎንደር ከተማ ቀበሌ 18 ልዩ ቦታው አየር ጤና ተብሎ በሚጠራው ቦታ የመብራትና ውኃ ወርሃዊ ክፍያ ለመክፈል የወጣችው የ26 ዓመት ወጣት ታገተች የሚል መረጃ ለሶስተኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል ምርመራ ቡድን ደረሰው ይላሉ የሶስተኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ ኀላፊ ምክትል ኮማንደር ደሳለኝ አበራ፡፡
ምክትል ኮማንደር ደሳለኝ አበራ እንደገለጹት የደረሳቸውን ጥቆማ በመቀበል ታገተች ወደተባለችው ልጅ ቤተሰቦች ቤት በመሄድ ስለተፈጠረው ችግር በዝርዝር ጠይቀው ሙያው የሚጠይቀውን ዘዴ ተጠቅመው የምርምራ ሂደቱ ቀጠለ ብለዋል፡፡
በምርመራ ሂደቱም አጋቹም ታጋቹም ግብረአበሩም ቤተሰቦች መሆናቸውን የሶስተኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል ምርመራ ቡድን አረጋግጧል፡፡
ተጠርጣሪዎችም የወንጀል ተግባሩን እንደፈጸሙት አምነዋል፡፡ በየቀኑ እየተደወለ ሶስት መቶ ሽህ ብር ክፈይ ካልሆነ ልጅሽን እንጎዳታለን የሚል ማስፈራሪያ የደረሳቸው የታጋች እናት ሁለት መቶ ሃምሳ ሽህ ብር በውጭ ሀገር ከሚኖሩ ልጆቻቸው በማስላክ በአምስት የተለያዩ ሰዎች ብሩን ከባንክ አውጥተው ከፍለዋል ብለዋል ምክትል ኮማንደር ደሳለኝ አበራ፡፡
ሆኖም ጉዳዩን በቅርብ ርቀት ሆኖ ሲከታተል የነበረው የሶስተኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል ምርመራ ቡድን ተጠርጣሪዎችንና ገንዘቡን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጿል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ አሁን ላይ በሕግ ጥላ ስር ውለው አስፈላጊው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሆነ ምክትል ኮማንደሩ ገልጸዋል፡፡
ህብረተሰቡም ካላስፈላጊ ድርድር ተቆጥቦ ከፖሊስ ጎን በመሆን ትብብር ሊያድርግ ይገባል ብለዋል ምክትል ኮማንደር ደሳለኝ አበራ፡፡
ዘጋቢ፡- መሰረት ባየ- ከጎንደር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር የሚመራ የከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ቡድን በደቡብ ወሎ ዞን የተከናወኑ የልማት ተግባራትን እየተመለከቱ ነው።
Next articleበሰሜን ሸዋ ዞን ከ760 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት በመስኖ ለምቶ ለገበያ መቅረቡን የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለጸ፡፡