
በባሕር ዳር ከተማ በመብራት የአገልግሎት ክፍያ መጉላላታቸውን ደንበኞች ተናገሩ፡፡
የአማራ ክልል ኤሌክትክ አገልግሎት የጂፒኤስ የጋራ ቆጣሪ ማንበቢያን በመተግብር ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እየሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 05/2013 ዓ.ም (አብመድ) መምህርት ሠፊሀገር ሰንደቁ ይባላሉ፡፡ በባሕር ዳር ከተማ የቀበሌ 16 ነዋሪ ናቸው፡፡ የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት የባሕር ዳር ዲስትሪክት ቁጥር አንድ አገልግሎት መስጫ ማዕከል የወር ሂሳብ ለመክፈል ተራ እየጠበቁ አገኘናቸው፡፡
እነ መምህርት ሠፊሀገር ከአሁን በፊት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የሞባይል ባኪንግ ተጠቅመው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ ይከፍሉ ነበር፡፡ ሂሳቡ ተሰርቶ በወቅቱ ባንክ ባለመድረሱ ግን ማዕከሉ ድረስ ለመምጣት ተገደዋል፤ በአካል ማዕከሉ ተገኝተው ሲጠይቁ ደግሞ “የቆጣሪ ንባብ አልደረሰንም ሄዳችሁ አንብብቻሁ ተመለሱ” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ነግረውናል፡፡
በአማራ ክልል ኤሌክትክ አገልግሎት የባሕር ዳር ዲስትሪክት ቆጣሪ አስነብቦ ሂሳቡን አሰርቶ ወደ ባንክ ባለመላኩ ሁለትና ሦስት ጊዜ መመላለሳቸውን ተናግረዋል፤ ይህም ላልተፈለገ ወጭና ለእንግልት እየዳረጋቸው እንደሆነ ነው የነገሩን፡፡ “በየወሩ መክፈል ባለመቻላችን ተጠራቅሞ የሚመጣው ሂሳብ በትልቁ ቁጥር ስለሚባዛ መብራታችን ለመቆረጥ ምክንያት እየሆነ ነው” ብለዋል መምህርት ሠፊሀገር፡፡
በባሕር ዳር ከተማ የቀበሌ 13 ነዋሪው አቶ መሰረት አድነው እንዳሉን ካሁን በፊት የሂሳብ ስሌቱ ተጠናቆ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በሞባይል ባንኪንግ እና በሲቢኢ ብር በመክፈላቸው አመች ነበር፡፡ ነገር ግን ቆጣሪ አንባቢው መጥቶ ቢያነብም ሂሳቡ ተሰርቶ ባለመላኩ ማዕከሉ ላይ ተገኝተው ሂሳብ ለማሠራት መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡
“ጊዜ ሀብት ነው፤ ነገር ግን እነሱ ባላጠናቀቁት ሥራ እኛ ሁለትና ሦስት ጊዜ እንድንመላለስ ተገደናል፤ ምልልሱ አሰልች በመሆኑ የሁለትና የሦስት ወር አንድ ጊዜ የሚከፍለው ሰው በርካታ ነው፤ በዚህም ላልተፈለገ ወጭ እየተዳረግን ነው” ብለዋል አቶ መሰረት፡፡
እንደ አቶ መሰረት አስተያየት መንግሥትም በሰዓቱ ማግኘት ያለበትን ገቢ እያገኘ አይደለም፤ በተጨማሪ በርካታ ሰው ሲገፋፋ ለኮሮና ቫይረስ የመጋለጥ እድል እየሰፋ ነው፤ ስለዚህ ማዕከሉ ቀላል የሆነ አሠራሮችን በመዘርጋት ችግሩ የሚቃለልበትን ሁኔታ ሊያመቻች ይገባል፡፡
ሌላዋ አገልግሎት ፈላጊ ወጣት ቤተልሔም ደምሴ በበኩሏ የመብራት አገልጎሎት ክፍያ ከመጣ 3 ወራት አልፏል፡፡ ሂሳቡን አሠርተው ለመክፈል ብትመጣም የሚያስተናግድ አለማግኘቷን ነግራናለች፡፡ በተጨማሪ “ከሰዓት አንሠራም” የሚሉበት ጊዜ በመኖሩ በምልልስ ጊዜአቸው እየባከነ እንደሆነ በምሬት ገልጻለች፡፡ እንደ ቤተልሄም አስተያየት እድሜያቸው የገፋ ሰዎች ተመላልሰው ለመክፈል አይችሉም፤ ይህ አሠራር መስተካከል አለበት፡፡
በአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት የባሕር ዳር ዲስትሪክት ቁጥር አንድ አገልግሎት መስጫ ማዕከል ሥራ አስኪያጅ አቶ መንግሥቱ ወርቅነህ በጉዳዩ ላይ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ እንደ ሥራ አስኪያጁ መረጃ ማዕከሉ ደንበኞችን ለማስተናገድ የጊዜ ሰሌዳ አውጥቷል፤ ነገር ግን በበዓል ሰበብ ደንበኞች ተራቸውን ጠብቀው ባለመምጣታቸው መጨናነቅ ተፈጥሯል፤ በተጨማሪ ደንበኞች ለመክፈል ሲመጡ “አሁን እስከቆጠረበት መክፈል እንፈልጋለን” በሚል አዲስ ሒሳብ እንዲሠራ ይፈልጋሉ፤ ይህ ደግሞ ወረፋ ይፈጥራል፡፡
“ደንበኞች ወሩን ጠብቀው ባለመክፈላቸው የተጋነነ ክፍያ ይመጣል፤ በዚህ የተጋነነ ዋጋ ምክንያት መብራታቸው እንዳይቋረጥና ለእንግልት እንዳያዳረጉ የቅስቀሳ እና የቆረጣ ቅጠላ ሥራ እንሠራለን” ብለዋል አቶ መንግሥቱ፡፡
አዳዲስ ቆጣሪዎች ደንበኛው ከተጠቀመበት በላይ የሚቆጥሩበት አጋጣሚ መኖሩን ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል፤ እንደነዚህ አይነት ችግሮች ሲያጋጥሙ ደንበኞች ለማእከሉ በማመልከት ቆጣሪ እንዲቀየርላቸው ማድረግ አለባቸውም ብለዋል፡፡ ወሩ በገባ ከ 19ኛው ቀን ጀምሮ ባሉ ተከታታይ ስድስት ቀናት ከሰዓት በኋላ ከፍተኛ የኃይል ተጠቃሚ ደንበኞች የሚስተናገዱበት በመሆኑ ደንበኞች ለክፍያ መምጣት እንደማይጠበቅባቸውም ጠቁመዋል፡፡
የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ኮምዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ማተቤ አለሙ እንዳሉት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የክፍያ ስርዓቱን ዘመናዊ ለማድረግ የተለያዩ አማራጮችን እየተጠቀመ ነው፡፡ እነዚህም ዘዴዎች የጥሬ ገንዘብ እና የሂሳብ ተቀናሽ በባንክ የሚከፈሉ ሲሆን የቀጥታ ከሂሳብ ተቀናሽ፣ ሲቢኢ ብር እና ኢንተርኔት ባንኪንግ ደንበኞች ባሉበት ሆነው የሚከፍሉባቸው አማራጮች ናቸው፡፡ ደንበኞች እነዚህን አማራጮች ተጠቅመው መክፈል እንደሚችሉም ጠቁመዋል፡፡
“አዲሱን አሠራር ተግባራዊ ስናደርግ ክፍያ ያለመድረስ ችግር ገጥሞን ነበር አሁን ተስተካክሏል፤ አሁን ባለን መረጃ በባንክ የሚሰጠው አገልግሎት አልተቋረጠም፡፡ ደንበኞች የሂሳብ ማሳወቂያ በእጅ ስልካቸው እንዲደርሳቸው ለማዕከሉ የሞባይል ቁጥራቸውን መስጠት ይጠበቅበቀቸዋል” ብለዋል፡፡ ዘመናዊ አሠራርን መከተል ደንበኞች የበለጠ ተጠቃሚ መሆናቸውን አቶ ማተቤ ገልጸዋል፡፡ ስለዚህ ደንበኞች የተቀመጡትን አማራጮች በመጠቀም የራሳቸውንም ሆነ የማዕከሉን የሥራ ጫና መቀነስ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
በአገልግሎት መስጫ ማዕከላት ከዚህ በፊት ቆጣሪ በግምት ሚሞላበት አጋጣሚ እንደነበር የጠቀሱት የኮምዩኒኬሽን ኃላፊው ችግሩን ለመቅረፍ የጂፒኤስ (CNRI) የጋራ ቆጣሪ ማንበቢያ በአገልግሎት መስጫ ማእከላት ተግባራዊ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም በቀጣይ ለደንበኞች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ