
በአለም ጤና ድርጅት ምዘና በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ከሚያደርጉ ሰዎች ውስጥ ቫይረሱ የሚገኝባቸው ሰዎች ከ10 በመቶ በላይ መሆኑ ሀገሪቱ የጤና አደጋ እንዲገጥማት ማድረጉ ተገለፀ።
ባሕር ዳር፡ ጥር 05/2013 ዓ.ም (አብመድ) የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እየተስፋፋና መዘናጋቶችም እየጨመሩ መሆኑን ተከትሎ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል የመልበስ ዘመቻ
” እንድናገለግለዎ ማስክወን ያድርጉ!!” በሚል መሪ መልዕክት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኀላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ ቫይረሱ እንደ ሀገር እያደረሰ ያለው ጉዳት እየሰፋ ቢሆንም በአዲስ አበባ ደግሞ የከፋ መሆኑን አንስተዋል። እንደ ሀገር ከተመዘገበው የሞት ቁጥር 72 በመቶ የሚሆነው ከተማ አስተዳደሩ ላይ የተመዘገበ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል የመልበስ ምጣኔም ከ75 በመቶ ወደ 54 በመቶ ቀንሷል ብለዋል ኀላፊው። በመሆኑም ወረርሽኙ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ሁሉንም የሚያሳትፍ ዘመቻ በሁሉም ክፍለ ከተሞች እንደሚካሄድ ገልፀዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በመጨመሩ የመተንፈሻ መሳሪያ እገዛ የሚያስፈልጋቸው ወገኖች በወረፋ መስተናገድ ጀምረዋል ነው ያሉት።
የሚገለፀው ቁጥርም ተመርምሮ የታወቀው እንጅ የወረርሽኙ መስፋፋት አስከፊ ሆኗል ብለዋል። በቫይረሱ በመያዝም በምትና በፅኑ ህሙማን ቁጥር አዲስ አበባ ከሁልም የበለጠ ተጎጂ መሆኗን ጠቅሰዋል።
የሚሰጡ ምክረ ሀሳቦች በማህበረሰቡ እየተተገበሩ አይደለም፤ ከወራት በፊት የነበረው መረዳትና ጥንቃቄ አሁን በሚያስደነግጥ ሁኔታ ቀንሷል ብለዋል። ይህንን ለመቀልበስ ከመሪዎች ጀምሮ መስራትና ለአንድ አካል ብቻ የሚሰጥ ሳይሆን የሁሉንም ድርሻ የሚጠይቅ እንደሆነ ተናግረዋል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በማስጀመሪያ መርሀ ግብሩ ላይ የመከላከል ሥራዎች በመሠራታቸውና የህክምና አገልግሎቱም በመኖሩ የከፋ ጉዳት ሳይደርስ ቆይቷል ብለዋል።
አሁን ግን በከፍተኛ መዘናጋት ምክንያት ከ128 ሺህ በላይ ሰዎች ተይዘዋል። ከ2 ሺህ በላይ የሚሆኑትም ህይወታቸውን አጥተዋል ብለዋል።
ከሚመረመሩት ሰዎች ውስጥም ቫይረሱ የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር ከ10 በመቶ በላይ በመሆኑ በአለም ጤና ድርጅት ምዘና አደጋ ውስጥ ያለን መሆኑን ጠቁመዋል።
የማስክ ማድረግ ንቅናቄው በሁሉም ክልሎች እንደሚተገበርም ተናግረዋል። አገልግሎት መስጫ አካባቢዎች በልዩ ትኩረት በንቅናቄው ልዩ ትኩረት ይሰጣቸዋል ነው የተባለው። ማኀበረሰቡም ይህንን በማክበር የመከላከል ሥራውን ማገዝ እንዳለበት ተጠቅሷል። የፀጥታ መዋቅሩም ይህንን የማስፈፀም ኀላፊነት እንዳለባቸው ተመላክቷል።
ዘጋቢ:– ዘመኑ ታደለ –ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ