“ተገቢዉን ድጋፍና እንክብካቤ ቢደረግለት ጣና ከሁለት ዓመታት በኋላ አይለምንም” የጣና ሐይቅና ሌሎች የውኃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ

165
“ተገቢዉን ድጋፍና እንክብካቤ ቢደረግለት ጣና ከሁለት ዓመታት በኋላ አይለምንም” የጣና ሐይቅና ሌሎች የውኃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ
ባሕር ዳር፡ ጥር 05/2013 ዓ.ም (አብመድ) በጣና ሐይቅ ዙሪያ ስምንት ወረዳዎችንና 30 ቀበሌዎችን አካልሎ የነበረው የእምቦጭ አረም ከአምስት ቀበሌዎች በስተቀር በ25 ቀበሌዎች (85) በመቶ አረሙ ተጠርጎ ዳር እንደተቀመጠ የውኃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ አስታውቋል።
በቀሩት አምስት ቀበሌዎች፣ ፍርቃዳንጉሬ፣ ሽሃጎመንጌ፣ ለምባ፣ ተዘባና ፈንታይ አረሙን የማስወገድ ሥራዉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ኤጀንሲው ገልጿል።
የተወገደው አረም ከሀይቁ ዳርቻ ላይ እንዲከማችና እንዲደርቅ ቢደረግም ከቦታው ካልተወገደ ከመሬቱ እርጥበት በማግኘት በክረምት ወራት በጎርፍ አማካኝነት ተመልሶ ወደ ሐይቁ ሊመለስ እንደሚችል የአብመድ የጋዜጠኞች ቡድን በሥፍራው ተገኝቶ ተመልክቷል።
አረሙን የሚያስወግዱ ሰዎች ቁጥራቸው በመቀነሱ ደግሞ አረሙን ለማስወገድ የሚደረገው ርብርብ ሊያራዝመው እንደሚችል የአካባቢዉ ሰዎች ተናግረዋል።
ወይዘሮ እነዬ ተስፋው በጎንደር ዙሪያ ወረዳ የሸሀጎመንጌ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። በጣና ሐይቅ ላይ የተንሰራፋውን የእምቦጭ አረም ለማስወገድ ርብርብ ከሚያደርጉ ሰዎች ውስጥ አንዷ ናቸው። በአካባቢያቸው የእምቦጭ አረም ጣናን በመውረሩ ምርትና ምርታማነት እንደቀነሰባቸው፣ ጣና በአረሙ በመታፈኑ ድሮ ሲያገኙት የነበረውን ቀዝቃዛ አየር እንደአጡም ተናግረዋል።
ዛሬ ግን ጠላት የሆነውን አረም ለማስወገድ ርብርብ ቢያደርጉም ለጽዳት የሚውሉ ቁሳቁስ፣ ለጥንቃቄ የሚውሉ አልባሳት እና የህክምና አገልግሎት አግኝተው እንደማያውቁ አስረድተዋል። ቀደም ሲል በቀን 150 ብር ሲከፈላቸው እንደቆየ ያስታወሱት
ወይዘሮ እነዬ አሁን ግን በቀን 75 ብር ብቻ እንደሚከፈላቸው ተናግረዋል።
በዚህ ምክንያት አረሙን ለማጥፋት ርብርብ ሲያደርጉ የነበሩ ሰዎች ቁጥራቸው በእጅጉ እንደቀነሰ ተናግረዋል። “እኛ ወትሮም ቢሆን ሕይወታችንና እንጀራችን የሆነውን ጣና ለመታደግ እንጂ ብር ለማግኘት አይደለም” ያሉት ወይዘሮ እነዬ አረሙን ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት በገንዘብ ማነስ ምክንያት የቀሩ ሰዎችን ኮንነዋል።
ሌላው የሸሃጎመንጌ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ጌጡ ወረታው አረሙ ጠላታቸው ስለሆነ ከገንዘብ ክፍያ አስቀድሞም በራሳቸው ተነሳሽነት ሲሠሩ እንደነበረ ተናግረዋል። ሆኖም አረሙን በማስወገድ ሂደት ውስጥ አልቄት ደማቸውን እንደሚያፈስ፣ ሰውነታቸውን እንደሚያሳክካቸው አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በእባብ እንደሚነደፉ ጭምር ተናግረዋል።
ይህ ሁሉ ችግር ቢኖርም ምንም አይነት የህክምና አገልግሎት እንደማያገኙ አስረድተዋል። አቶ ጌጡ “ጣና መኖሪያችን ስለሆነ ሕይወታችን እስከ መስጠት አረሙን እንዋጋዋለን፣ መንግሥትም ድካማችን አይቶ ለአረም ማስወገጃ የሚውል አልባሳት፣ ሳሙና፣ ቅባትና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁስ ድጋፍ ሊያደርግልን ይገባል” በማለት ጠይቀዋል።
በጣና ሐይቅ ላይ የተንሰራፋዉን የእምቦጭ አረም ለማስወገድ በሚደረገው ዘመቻ የሰው ጉልበትን ጨምሮ የተለያዩ አጋዥ ማሽኖች እየሠሩ ቢገኙም አንዳንድ ማሽኖች ግን ያለ ሥራ መቆም እንደሚያበዙ ያነጋገርናቸው የአካባቢዉ ነዋሪዎች መስክረዋል።
የጣና ሐይቅና ሌሎች የውኃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ አያሌው ወንዴ (ዶክተር) አረሙ በአሁኑ ሰዓት 85 በመቶ መወገዱን ተናግረዋል፡፡ ሥራ አስኪያጁ ባደረጉት ንግግር አረሙ በ25 ቀበሌዎች ተወግዶ የቀረው ሥራ ማቃጠል ብቻ ነው። በተያዘው የበጋ ወቅት አረሙ እየተገላበጠ ከደረቀ በኋላ ሲቃጠል ተመልሶ ሊያንሰራራ እንደማይችል ዶክተር አያሌው አረጋግጠዋል። አረሙ በጸዳበት ቀበሌዎች የለቀማ ሥራን የሚሠሩ ሰዎች የተመደቡ መሆኑንም ገልጸዋል።
በሥራ ቦታ የሚገኙ ማሽኖች በሙሉ አቅማቸው እየሠሩ አለመሆኑንም ዶክተር አያሌው ነግረውናል። “ከአሁን በፊት የማሽኖችን ኦፕሬሽን የሚያስተባብር ሠራተኛ የዲሲፕሊን ግድፈት በመፍጠሩ ከሥራ በማገድ በምትኩ ለዘርፉ የሚመጥን ሌላ ሠራተኛ መድበናል” ያሉት ሥራ አስኪያጁ ዘርፉ ተደጋጋሚ ችግር ስለሚስተዋልበት የራሱ የሆነ ክትትል ሊያደርግ የሚችል መዋቅር ሊዘረጋለት እንደሚገባ ገልጸዋል።
በሥራ ላይ የሚገኙ ሰዎች ጤንነታቸው እንዲጠበቅ በፊት ለጽዳት የሚያገለግሉ ቁሳቁስ ተሰጥተው እነደነበረ ሥራ አስኪያጁ አስታውሰዋል። ሆኖም ተጨማሪ ለጽዳት የሚውሉ ቁሳቁስ፣ ለሥራዉ የሚውሉ አልባሳት፣ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ኤጀንሲው አቅም እንደሌለው አስረድተዋል።
ጣና ወደፊት የራሱ የሆነ ገቢ ሊያመነጭ እንደሚችል ያመላከቱት ዶክተር አያሌው “ተገቢዉ ድጋፍና እንክብካቤ ቢደረግለት ጣና ከሁለት ዓመታት በኋላ አይለምንም” ብለዋል።
“አረሙን ለማጥፋት ርብርብ ለሚያደርጉ የአካባቢው ነዋሪዎች በፊት በቀን 150 ብር ነበር የምንከፍላቸው አሁን ግን አቅም ስለሌለን 75 ብር ብቻ ነው እየከፈልናቸው የምንገኘው።
ይሁን እንጂ የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራዉ ውጤት የራሳቸው በመሆኑ እንዲሁም የዜግነት ግዴታ በመሆኑ በጀት ብንጨርስ እንኳ ቀድሞ እንደተለመደው በነፃም ቢሆን ሊያገለግሉ ይገባል” ያሉት ሥራ አስኪያጁ አረሙን ለማጥፋት ድጋፍ ለመስጠት ቃል የገቡ አጋር ድርጅቶች ቃላቸውን ሊያከብሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በጣና ሐይቅ ላይ የተንሰራፋውን የእምቦጭ አረም እስከመጨረሻ ለማስወገድ ከሦስት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ያስፈልጋል። አሁን ግን በ85 ሚሊዮን ብር ብቻ ሥራዉ እየተካሄደ እንደሆነ ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“በየአመቱ በአማካይ ከ14 ሺህ በላይ እናቶች በወሊድና ከወሊድ ጋር በተገናኘ ህይወታቸውን ያጣሉ” ዶክተር ሊያ ታደሰ
Next articleጎንደር ለአስመራ ጥሪ አደረገች።