በማይካድራው የዜጎች ጭፍጨፋ ወንጀል የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦችና ተባባሪዎቻቸው ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡

403
በማይካድራው የዜጎች ጭፍጨፋ ወንጀል የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦችና ተባባሪዎቻቸው ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 04/2013ዓ.ም (አብመድ) በማይካድራ ዜጎችን ሲያስጨፈጭፉ ነበሩ የተባሉ ሁለት ተጠርጣሪዎችና ሦስት ተባባሪዎቻቸው ዛሬ የፌዴራሉ መካከለኛ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ቀርበዋል።
ሁለቱ ተጠርጣሪዎች በማይካድራ ንጹሓን ዜጎች እንዲጨፈጨፉ ካስደረጉ በኋላ ሸሽተው አዲስ አበባ ገብተው ከተሸሸጉበት የእንግዳ ማረፊያ ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት።
በዚህ ወንጀል ተጠርጥረው ዛሬ ፍርድ ቤት የቀረቡት ተስፋይ ከበደ እና አባዲት አብርሃ ሲሆኑ እነሱን በመሸሸግ ተባባሪ ናቸው የተባሉት ደግሞ ኪዳኔ ገብረሕይወት፣ ሙሉአለም ዩሃንስ እና ፍሬሰንበት ለማ ናቸው።
መርማሪ ፖሊስ ዛሬ ለፍርድ ቤቱ እንዳቀረበው በተጠርጣሪዎቹ ላይ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ሲያሰባስብ የቆየ መሆኑን አስረድቷል። በመሆኑም እስካሁን በተካሔደው የምርመራ ሥራ የተጠርጣሪዎችን ቤት በመፈተሽ ማስረጃዎችን ማሰባሰቡን አመልክቷል።
በአሁኑ ወቅት ማስረጃዎችን ለቴክኒክ ምርመራ ወደ ሚመለከተው አካል መላኩን ጠቁሞ ቀሪ ሥራዎችን ለማከናወን ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል።
ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው መርማሪ ፖሊስ ማስረጃዎችን እስኪሰበስብ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርና በውጭ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ጠይቀዋል።
የግራ ቀኝ ክርክሩን ያደመጠው ፍርድ ቤቱ ግን የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ መርማሪ ፖሊስ ከጠየቀው 14 ቀን ውስጥ 11ዱን በመፍቀድ ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ኢዜአ ዘግቧል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየጎንደር ከተማ አስተዳደር ገቢዎች መምሪያ ዘመናዊ አሠራርን በመተግበሩ ግብር ከፋዮች ግብራቸውን በወቅቱ እንዲከፍሉ አስችሏቸዋል፡፡
Next article“በየአመቱ በአማካይ ከ14 ሺህ በላይ እናቶች በወሊድና ከወሊድ ጋር በተገናኘ ህይወታቸውን ያጣሉ” ዶክተር ሊያ ታደሰ