ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች ከአንድ ቢሊዮን 300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ፡፡

211
ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች ከአንድ ቢሊዮን 300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 04/2013 ዓ.ም (አብመድ) ባለፉት ስድስት ወራት ወደ ውጪ ከተላኩ የተለያዩ ምርቶች ከአንድ ቢሊዮን 300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ። ሚኒስቴሩ የዘርፉን የግማሽ ዓመት አፈፃፀም ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ ከተማ እየገመገመ ነው።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋናው አረጋ በግምገማው መድረክ እንዳሉት ገቢው ከተገኘባቸው ምርቶች መካከል ወደ ውጭ የተላኩ ቡና፣ ቅመማ ቅመም፣ ጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎች ይገኙበታል።
ከማዕድንና ኢንዱስትሪ ምርቶች የተገኘው የውጪ ምንዛሬ የተሻለ መሆኑም ተገልጿል።
የተገኘው ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም ከ224 ሚሊዮን በላይ የአሜሪካን ዶላር ብልጫ መገኘቱን አመልክተዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ የተሻለ አፈፃፀም ያለ ቢሆንም ሀገሪቱ ከውጪ ለምታስገባው የተለያዩ ምርቶች በዓመት ከ19 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ እያወጣች ነው። ሀገሪቱ ወደ ውጭ ከምትልካቸው ምርቶች በዓመት የሚገኘው ከ3 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር መዝለል አልቻለም ፤ አሁን ያለውን አቅምና አፈጻጸም ይዘን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ማሳካት አንችልም ብለዋል።
በተለይም በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ተወዳዳሪ ለመሆንና የሀገሪቱን ጥቅም ለማስጠበቅ በወጭ ምርቶች ጥራትና ብዛት ላይ መስራት እንደሚገባ አምባሳደር ምስጋናው ተናግረዋል።
የግብርናና ማኑፋክቸሪንግ የኢንዱስትሪ ምርቶችን የእሴት ሰንሰለት ውስጥ ማሳለፍ፣ የንግድና ግብይት ሥርዓትን ማዘመን፣ የተቋማት የቴክኖሎጂ አጠቃቀም አቅም ማጎልበት፣ ድጋፍና ክትትል ላይ በሙሉ አቅም መስራት ግብ ለማሳካት እንደሚረዳ ጠቅሰዋል።
በዚህም የመንግስትን እጅ መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ባለሃብቶች የሚያጋጥማቸውን ችግር በማቃለል በተለይም የአቅርቦት፣ መሬትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት መሰል መድረኮች ጠቃሚ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የተሻለ የሚደግፍና ለዜጎች የስራ ዕድል የሚፈጥሩ ሴክተሮች ልዩ ድጋፍ እንደሚሰጣቸውም ሚኒስትር ዴኤታው ማስታወቃቸውን ኢብኮ ዘግቧል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleአዲሱ የኮሮናቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ጥንቃቄ እየተደረገ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
Next article“በጥምቀት በዓል የትራንስፖርት አገልግሎት ችግር እንዳይገጥም በመናኸሪያዎች ላይ ክትትል እና ቁጥጥር እያደረኩ ነው” የአማራ ክልል መንገድ እና ትራንስፖርት ቢሮ