አዲሱ የኮሮናቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ጥንቃቄ እየተደረገ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

146
አዲሱ የኮሮናቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ጥንቃቄ እየተደረገ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 04/2013 (ኢዜአ) በአንዳንድ ሀገራት እየታየ ያለው አዲስ የኮሮናቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ አስፈላጊው ጥንቃቄ እየተደረገ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።
ከመስከረም 2013 ዓ.ም ጀምሮ አዲስ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ በእንግሊዝ መከሰቱ ይታወሳል፤ ይኸው ቫይረስ በአጭር ጊዜ ወስጥ አሜሪካና ካናዳም ገብቷል።
በደቡብ አፍሪካና በናይጄሪያም በእንግሊዝ አገር ከተገኘው የቫይረሱ ዝርያ የተለየና አዲስ አይነት የኮሮናቫይረስ ዝርያ በቅርቡ ተከስቷል።
የቫይረሱ ዝርያ ከመጀመሪያው ቫይረስ ጋር ሲነጻጸር የህመም ደረጃን የመጨመርም ሆነ ለሞት የማጋለጥ እድሉ ምን ያክል እንደሆነ በጥናት አልተረጋገጠም።
ያም ሆኖ አዳዲሶቹ የቫይረሱ ዝርያዎች በፍጥነት ከሰው ወደ ሰው የመዛመትና የመተላለፍ እድላቸው ከፍተኛ መሆኑን ነው መረጃዎች የሚያሳዩት።
በአሁኑ ወቅት እየወጡ ያሉ ጥናቶችም አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ቀደም ሲል ለቫይረሱ የተሰሩት ክትባቶች እንደሚከላከለው አመላክተዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ የኮሮናቫይረስ ዝርያዎች በፍጥነት ስለሚዛመቱ ለኢትዮጵያ ስጋት መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዴኤታዋ ሰሃረላ አብዱላሂ ተናግረዋል።
በተለይም በደቡበ አፍሪካና በናይጄሪያ የተገኙት የቫይረሱ ዝርያዎች ከቅርበት አንጻር ለኢትዮጵያ ስጋት ስለሚሆኑ ትኩረት ተደርጓል ብለዋል። ይህንንም ተከትሎ በተለይም ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡትን መንገደኞች የመመርመር ሥራ ተጠናክሮ እየተከናወነ መሆኑን ነው ያመላከቱት።
በድንበር አካባቢም ያለው የቁጥጥር ሥራ መጠናከሩንም ገልጸዋል።
የትኛውንም አይነት የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ለመከላከል በጤና ባለሙያዎች የቀረቡትን የመከላከያ ሥልቶች ተግባራዊ ማድረግ መፍትሄ መሆኑን ተናግረዋል።
እጅን በሳሙና መታጠብ፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ማድረግና አካላዊ ርቀትን መጠበቅ የሚሉትን መርሆች ሊከበሩ ይገባልም ነው ያሉት።
በተለይም አዲሱ የኮሮናቫይረስ ወጣቶችን ያጠቃል የሚል ጥናት መኖሩን ጠቁመው ወጣቶች ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በመጭው የጥምቀት በዓል ላይም ኅብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ጠቁመው ሁሉም ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የኮሮናቫይረስ በማኅበረሰቡ ውስጥ በስፋት ስለተሰራጨ ጥንቃቄው አብሮ ሊጎለብት ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ሱዳን በድንበር አካባቢ የምታደርገውን ሕገወጥ እንቅስቃሴ ቀጥላለች” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
Next articleወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች ከአንድ ቢሊዮን 300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ፡፡