
“ሱዳን በድንበር አካባቢ የምታደርገውን ሕገወጥ እንቅስቃሴ ቀጥላለች” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
ባሕር ዳር፡ ጥር 04/2013 ዓ.ም (አብመድ) ሱዳን በኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ የምታደርገውን ሕገወጥ እንቅስቃሴ መቀጠሏን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ።
ቃል አቀባዩ በአገሪቷ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የሣምንቱን አበይት የዲፕሎማሲ ክንውኖች አስመልክተው መግለጫ ስጥተዋል።
ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ከውጭ ኃይሎች ጋር ጦርነት ብታደርግም ነገር ግን ጦርነት ትርፍ እንደሌለው ትረዳለች ብለዋል። ኢትዮጵያና ሱዳን ወደ ግጭት እንዲገቡ በማድረግ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚሰሩ የተለያዩ ሶስተኛ ወገኖች ፍላጎት እንዳለ ገልፀው፤ ኢትዮጵያ የጦርነት አማራጭ እንደማትጠቀም አክለዋል።
የኢትዮጵያና ሱዳን ሕዝቦች ረጅም ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው በመሆናቸው የጋራ ዕድገት እንጂ ጦርነት እንደማይፈልጉም ነው የገለጹት። በአንፃሩ ሱዳን በድንበር አካባቢ አሁንም በተጠናከረ ሁኔታ ጦሯን እያንቀሳቀሰች መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ለሠላምና ዲፕሎማሲ ቅድሚያ ትሰጣለች ያሉት ቃል አቀባዩ፤ የሱዳን ጦር ወደ ድንበሯ ጥሶ በመግባት እያደረገ ያለውን ሕገወጥ እንቅሰቃሴ መታገሷ ከፍርሃትና ከመወላወል ጋር የተገናኘ እንዳልሆነ ገልፀዋል።
እ.አ.አ 1902 የተደረገውን ድንበር የማካለል ታሪክ ተከትሎ በተለያዩ ጊዜያት የተጀመሩ የጋራ የድንበር ማካለል ሠላማዊ እንቅስቃሴዎች በመመለስ የሁለቱን አገራት የድንበር ችግር መፍታት ተገቢ እንደሆነም መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ