
የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባ ምርትን የመተካት ሙሉ አቅም እንዳላቸው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 04/2013 ዓ.ም (አብመድ) የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ ሲገቡ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባ ምርትን የመተካት ሙሉ አቅም እንዳላቸው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ድኤታ አቶ እሸቴ አስፋው ተናግረዋል።
የንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስቴርና የአማራ ክልል የንግድና ገበያ ልማት እንዲሁም ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮዎች አመራሮች በቡሬ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ወደ ስራ የገቡ ፋብሪካዎችንና ፊቤላ የዘይት ፋብሪካን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ 97 በመቶ የግንባታ ስራው በተጠናቀቀው የቡሬ አግሮ ኢንደስትሪ በ7 የምርት አይነቶች የተሠማራው ሪችላንድ አግሮ ኢንዱስትሪና በዘይት ማምረትና የአልሚ ምግብ ዘርፍ የሚሠራው የቻይና ኩባንያ ወደ ስራ የገቡ መሆኑ ተገልጿል።
በ 4 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር የኢንቨስትመንት ወጭ ወደ ስራ እየገባ የሚገኘው እና በቀን 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ሊትር ዘይት በማምረት የሀገሪቱን የዘይት ፍላጎት 60 በመቶ እንደሚያሟላ የተነገረለት የፊቤላ የምግብ ማቀነባበሪያና የዘይት ፋብሪካም ተጎብኝቷል።
በኢንዱስትሪ ፓርኩና በዘይት ፋብሪካው የኃይል አቅርቦት ችግር፣የውጭ ምንዛሬ እጥረትና በሀገርውስጥ የግብርና ግብአቶች አቅርቦት ውስንነት ዘርፉን ሀገሪቱ ከውጭ የምታስገባቸውን ምርቶች ለመተካት የተያዘውን እቅድ በተሟላ እንዳይፈፀም እያደረጉ ያሉ ችግሮች እንደሆኑም ተመልክቷል።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ድኤታው አቶ እሸቴ አስፋው የአካባቢውን ፋብሪካዎች መሸከም የሚችል የኃይል ማከፋፈያ ንዑስ ጣቢያ(substation) ለመገንባት ስራዎች እየተጠናቀቁ በመሆናቸው ችግሩ እንደሚቃለል ተናግረዋል።
ከመደበኛ የመኸር ምርት ባለፈ መስኖን በማጎልበት የምርት አቅርቦትን ለማሳደግ፣ ከውጭ ዘይት ይገባበት የነበረውን የውጭ ምንዛሬ ወደ አልሚዎች በማስተላለፍ የምንዛሬ አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ እንደሚሠራም ሚኒስትር ድኤታው መግለጻቸውን የዘገበው ኢብኮ ነው።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ