
በምስራቅ ሸዋ ዞን በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት የተገነባው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመረቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 03/2013 ዓ.ም (አብመድ) በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በ20 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው ‘ኢፈ ሊበን’ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመረቀ።
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ሊበን ጩቋላ ወረዳ ጎንጎ ቀበሌ ለምረቃ የበቃው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ አንድ ዓመት የወሰደ ሲሆን በዚህ ዓመት 220 ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር ይጀምራል።
በክልሉ የዛሬውን ጨምሮ በሰሜን ሸዋ፣ በምዕራብ ሐረርጌና በምዕራብ ጉጂ ዞኖች በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት ወጪ የተገነቡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ወደ ሥራ ገብተዋል።
በተያዘው ዓመት በክልሉ ምዕራብ አርሲ፣ ምዕራብ ሸዋ፣ ምዕራብ ወለጋና ጅማ ዞኖች በጽሕፈት ቤቱ አማካኝነት ትምህርት ቤቶች እንደሚገነቡ ታውቋል።
በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት የሚገነቡ ትምህርት ቤቶች ረጅም ርቀት ተጉዘው የሚማሩ ተማሪዎች በአቅራቢያቸው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የማስቻልና የትምህርት ተደራሽነት የማስፋት ዓላማ ያላቸው ናቸው።
ጽሕፈት ቤቱ ትምህርት ቤቶች በሌሉባቸው አካባቢዎች ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ለአካባቢው ማኅበረሰብ እያስረከበ መሆኑ ተገልጿል።
በምርቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ፣ የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶና ሌሎችም የሥራ ኃላፊዎች መገኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ