
“የዳግማዊ አፄ ምኒልክ መታሰቢያ ሙዚየምና የባሕል ማዕከል በፍጥነት የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጥ የክልሉ መንግሥት በልዩ ትኩረት ይሠራል” የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ
ባሕር ዳር፡ ጥር 03/2013 ዓ.ም (አብመድ) ሸዋ የኢትዮጵያ የስልጣኔ መሠረት የተጠነሰሰባት ማዕከላዊ ሥፍራ ናት።
ለዚህም በሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶች፣ የታሪክ መዛግብትና ባሕላዊ ክዋኔዎች ማሳያዎች መሆናቸውን ነው የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ እንድሪስ አብዱ የተናገሩት።
የክልሉ መንግሥትም እነዚህ ታሪኮች፣ ባሕሎችና ወጎች እንዲሁም ታሪካዊና መንፈሳዊ ቅርሶች በአግባቡ ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ ሢሠራ እንደነበር አንስተዋል።
ይሁን እንጂ ሀብቱን ወደ ኢኮኖሚ ለመቀየር ብዙም እንዳልተሠራበት አመላክተዋል። ችግሩ በሰሜን ሸዋ ጎልቶ የሚታይ መሆኑን ያመላከቱት ምክትል ቢሮ ኀላፊው በምሥራቁ የአማራ ክልል አካባቢዎች ያለውን የቱሪዝም ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል እንዳልተቻለም አስታውቀዋል። ለዚህም ምክንያቱ ለዘርፉ ትኩረት አለመሰጠቱ መሆኑን ተናግረዋል።
የክልሉ መንግሥት ችግሩን በመረዳት በክልሉ ያለው የቱሪዝም ፍሰት እንዲጨምር ለማድረግ እየሠራ መሆኑንም ኀላፊው ለአብመድ ገልፀዋል።
በፌዴራል መንግሥት ለቀጣይ 10 ዓመታት በተዘጋጀው ፍኖተ ካርታ ዋንኛ የኢኮኖሚ ምንጭ እንዲሆኑ ከታቀዱት መካከል የቱሪዝም ዘርፉ አንዱ ነው፤ የክልሉ መንግሥትም የእቅዱ አካል አድርጎ በትኩረት እንደሚሠራበት አመላክተዋል።
በተያዘው ዓመት የዓለም የቱሪዝም ቀን ሲከበር ከሸዋ እስከ ወሎ በሚል መርህ የተመሠረተ ነበር። ይህም በምሥራቁ የአማራ ክልል አካባቢዎች ያሉ የቱሪዝም ሀብቶች፣ ባህሎች፣ ትውፊቶችና ወጎች በአግባቡ እንዲተዋወቁ ጥሩ ጅምር እንደሆነ አረጋግጠዋል።
በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ሰፊ የቱሪዝም ሀብት መኖሩን በመጥቀስም የማልማት ሥራው በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በአንኮበር ወረዳ በ6 ሚሊዮን ብር ተገንብቶ ጥር 02/2013 ዓ.ም የተመረቀው ዘመናዊ ሙዚየም የኢትዮጵያን ታሪክ በአግባቡ በማስተዋወቅ፣ ለቀጣይ ትውልድም በማስተላለፍ ዕቅዱን ለማሳካት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው አብራርተዋል።
የሙዚየሙ መገንባት፣ በሙዚየሙ የሚደራጁ ቅርሶች፣ ታሪኮች፣ እሴቶችና ሁለንተናዊ ተግባራት ትክክለኛውን ታሪክ በማስተማር ለዓመታት የተሠራውን የሀሰት ትርክት ከመሠረቱ ለመንቀል እንደሚረዳ አስረድተዋል።
የዳግማዊ አፄ ምኒልክ መታሰቢያ ሙዚየምና የባሕል ማዕከል በአማራ ክልል መንግሥት የተገነባ ሁለተኛው ሙዚየም ነው። በደንብ ቁጥር 186/2011ዓ.ም የተቋቋመው ሙዚየሙ በቦርድ እየተመራ ሥራውን ይቀጥላል ብለዋል። በፍጥነት የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጥም የክልሉ መንግሥት በልዩ ትኩረት ይሠራል ብለዋል።
ከወረዳው ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ቅርሶች የሚገኙት በተቋማትና በግለሰቦች እጅ ነው። አቶ እንድሪስም ይህንኑ አረጋግጠዋል። እነዚህ ቅርሶች ተገቢው ጥበቃ እንዲደረግላቸው ብሎም ከኢኮኖሚያዊ ትሩፋታቸው ለመጠቀም ይቻል ዘንድ ወደ ሙዚየሙ ማስገባት ይጠይቃል ብለዋል።
ለዚህም ማኅበረሰቡ በስጦታ መልክ በማቅረብ የድርሻውን ሚና እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል። መንግሥትም የተለያዩ የአሠራር ሥልቶችን ተጠቅሞ ቅርስ የማሰባሰብ ሥራውን እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
ሙዚየም ማልማት ከፍተኛ ሀብት የሚጠይቅ ቢሆንም ለታሪክና ለማንነት ቅድሚያ በመስጠት በሌሎች አካባቢዎች ተጨማሪ ሙዚየሞችን የማልማት ሥራው ይቀጥላል ነው ያሉት አቶ እንድሪስ። ይህ የሚሆነው ግን ሁለቱ ሙዚየሞች በሙሉ አቅማቸው ሥራ ከጀመሩ በኋላ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለያዩ ከተሞች የባሕል ማዕከላት እየተገነቡ መሆኑንም አስታውቀዋል፤ይህም በቀጣይ ዓመታት የአማራ ክልልን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማሳደግ እንደሚያስችል ታምኖበታል።
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ