አማራ ክልል 3 ሚሊዮን ገደማ ለሚሆኑ ዜጎች የዕለት ደራሽ ምግብ እያቀረበ መሆኑን የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን አስታወቀ።

420
አማራ ክልል 3 ሚሊዮን ገደማ ለሚሆኑ ዜጎች የዕለት ደራሽ ምግብ እያቀረበ መሆኑን የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን አስታወቀ።
ባሕር ዳር፡ ጥር 03/2013 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ወቅታዊ የተፈናቃዮችን መረጃ በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዘላለም ልጃለም ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ከኦሮሚያ፣ ከቤኒ ሻንጉል ጉሙዝ፣ ከደቡብ እና ከትግራይ ክልል ለተፈናቀሉ 271 ሺህ በላይ ዜጎች 41 ሺህ ኩንታል በላይ የዕለት ደራሽ ምግብ እየደረሰ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ከእነዚህ ዜጎች በተጨማሪ ደግሞ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋ ለደረሰባቸው ዜጎች ክልሉ በአጠቃላይ 413 ሺህ ኩንታል በላይ የዕለት ደራሽ ምግብ በየወሩ እያቀረበ እንደሚገኝ ኮሚሽነር ዘላለም ልጃለም ተናግረዋል። ድጋፉ ከክልሉ መንግሥት፣ ከፌዴራል መንግሥት እና ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር በቅንጅት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ይህም ሆኖ ሰፊ ችግር እንዳለ ኮሚሽነር ዘላለም በመግለጫቸው አንስተዋል። የተደራሽነት እና የፍትሐዊነት ችግሮች በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ።
ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው በሌላ ክልል በሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ላይ የደረሰው መፈናቀል ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እያስከተለ እንደሚገኝም ተናግረዋል። ኮሚሽኑ ለተፈናቃዮች የንፁህ መጠጥ ውሃ፣ መጠለያ እና አልባሳት ለማድረስ ጥረት እያደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
የረጂ ድርጅቶች እና የመንግሥት ቅንጅታዊ ሥራ በአግባቡ አለመካሄድ አንዳንድ ግለሰቦች እና ድርጅቶች በግል በመሄድ ለተፈናቃዮች ድጋፍ ለማድረስ በሚያደርጉት ሙከራ የፀጥታ እና የፍትሐዊነት ችግር እንዲፈጠር እያደረጉ መሆኑን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
የተፈጠሩ የአሠራር ክፍተቶችን ለመሙላት የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል ስለተቋቋመ እርዳታ ማድርግ የሚሹ ዜጎችም በማስተባበሪያ ማዕከሉ በኩል ማለፍ እንዳለባቸው ተናግረዋል። ዜጎችን ወደ ተፈናቀሉበት አካባቢ ለመመለስ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን የገለፁት ኮሚሽነሩ በአካባቢው ዘላቂ ሠላም ሲረጋገጥ ወደ ቀያቸው ይመለሳሉ ብለዋል።
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleከ290 ሽህ ዶላር በላይ የህክምና ቁሳቁስ ተበረከተ፡፡
Next article“የዳግማዊ አፄ ምኒልክ መታሰቢያ ሙዚየምና የባሕል ማዕከል በፍጥነት የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጥ የክልሉ መንግሥት በልዩ ትኩረት ይሠራል” የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ