
የህጻናትን ፍልሰት ለመከላከል ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 02/2013 ዓ.ም (አብመድ) የሕጻናትን ፍልሰት ለመከላከል ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ፡፡ የሕጻናትን ፍልሰት ችግር በሁሉም ከተሞች ቢሆንም ለአብነት ባሕር ዳር ከተማ የገብያ አካባቢዎች ጎራ ያለ ሰው “የሚያዝ አለ፣ ልያዛት፣ ልያዘው” የሚሉ እድሜያቸው ለሥራ ያልደረሱ ህጻናትን ጥያቄ መስማት የተለመደ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ መሸከም የማይችሉትን ለመሸከም ከባለቤቱ ጋር ሲደራደሩ ይስተዋላል፡፡
ከአቅማቸው በላይ ተሸክመው የሚታዩ ህጻናትም ብዙዎች ናቸው፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ በልቶ ለማደርና የዕለት ፍላጎታቸውን ለመሸፈን ነው፡፡ ከሸማቹ ጋርም በዋጋ ሲነጋግሩ የወቅቱን የኑሮ ውድነት ያነሳሉ “ዛሬ አንድ ዳቦ ስንት ነው? እንጀራስ?” ብለው ሌላ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡
በገብያ አካባቢዎች ዘንቢል አንጠልጥሎ ወደ ገበያ የገባን ሰው ተከትለው የሚዞሩ “ስገዛ ትሸከምልኛለህ” ተብለው ቃል የተገባላቸው የሚመስሉ ሕጻናትም ይስተዋላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ የሸማቹን መዘናጋት ጠብቀው እጃቸውን ወደ ሰው ቦርሳ የሚልኩም አይታጡም፡፡
ለዚህ ሁሉ መዘዙ ደግሞ ሕገ ወጥ የህጻናት ፍልሰት ነው፡፡
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ የህጻናት ደኅንነት ማስጠበቅ ዳይሬክተር አቶ አሻግሬ ዘውዴ ከአብመድ ጋር በስልክ ቆይታ አድርገዋል፡፡ አቶ አሻግሬ እንዳሉት የአማራ ክልል ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ አስከፊውን የህጻናት ዝውውር ለመከላከል ጥረት ቢያደርግም ለውጥ ማምጣት እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ህጻናትን በማሰባሰብ ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ትምህርት የሚሰጥበት ማዕከል አለመኖር በየጊዜው ከቤተሰቦቻቸው የሚቀላቀሉ ህጻናት ተመልሰው እንዲፈልሱም ምክንያት ሆኗል ብለዋል፡፡ ህጻናት አካባቢያቸውን ለቀው ለመሄድ በርካታ ምክንያት ቢኖራቸውም የቤተሰብ ድህነት፣ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች፣ የአቻ ግፊት፣ የወላጅ እጦትና የተሻለ ኑሮ ፍለጋ በዋናነት የሚጠቀሱ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል፡፡
ይሁን እንጅ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ለህጻናት የተስፋ ቃል በመስጠት፣ ዛቻ፣ አስገድዶ በማገድና ኀይል በመጠቀም ህጻናትን ከቦታ ቦታ ያዘዋውሯቸል፡፡ ይህ ጉዳይ በወንጀል የሚያስጠይቅ ቢሆንም ሥራውን በድብቅ በመሥራታቸው በርካታ ህጻናት በከተሞች ሲንቀሳቀሱና ለችግር ሲዳረጉ ይታያል፡፡
ይሄን ችግር ለመቅረፍ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ ባሉ ጊዜያት 30 ሺህ 186 ህጻናትን ወደ ቤተሰቦቻቸው የማቀላቀል ሥራ መሠራቱን አቶ አሻግሬ ተናግረዋል፡፡ በ2012 ዓ.ም መጋቢት ወር ጀምሮ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወደ ሀገሪቱ መግባቱን ተከትሎ 6 ሺህ 348 ህጻናትን ወደ መጡበት አካባቢ የመመለስ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል፡፡
ህጻናት በብዛት የሚፈልሱበትን አካባቢ መለየቱን የነገሩን ዳይሬክተሩ ችግሩን በዘላቂነት ለማስቆም የሁሉንም ትብብር እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል፡፡ የሕጻናትን ፍልሰት ከምንጩ ለማድረቅም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመምከርም ቢሮው እቅድ መያዙን አቶ አሻግሬ አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ