‹‹ግራካሱ ልውጣ ዳገቱን አልፌ፣ የእናት ጡት ማለት ነው የኮረም ኮረፌ››

954
‹‹ግራካሱ ልውጣ ዳገቱን አልፌ፣
የእናት ጡት ማለት ነው የኮረም ኮረፌ››
ባሕር ዳር፡ ጥር 02/2013 ዓ.ም (አብመድ) የግራ ካሱ ተራራ በኩራት ቆሟል፡፡ በአላማጣ የነበረችው ሞቃት ፀሐይ በግራ ካሱ የለችም፡፡ ሙቀቷን ያ አስፈሪ ተራራ ወስዶባታል፡፡ አካባቢው ቀዝቃዛ ሆኗል፡፡ ለወትሮው አስፈሪ የሆነው ግራ ካሱ በሕግ ማስከበሩ የነበረበት አያሌ ውጊያ ሌላ አስፈሪ ነገር ጨምሮበታል፡፡ እንደ መልካም ሰፊ ስፌት በተጥመዘመዘው የግራ ካሱ መንገድ ከአላማጣ ተነስተው ወደላይ ሲሄዱ አጀብ ያሰኛል፡፡ ያን ሁሉ የመሳሪያ ድምፅ እንዳልሰማ ዝምታን መርጧል፡፡ ውጊያ እንደነበረበት የሚመሰክር የተቆፈረው ምሽግ ነው፡፡
የሀገር መከላያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በዚያ አስቸጋሪ ስፍራ የትህነግን ቡድን የደመሰሱበት ጀብዱ ሲታሰብ ይሄስ ድንቅ ነው ያስብላል፡፡ ከምሽግ ምሽግ ተደራርቦበት የነበረው የግራ ካሱ ተራራ እንኳንስ በውጊያ በሰላማዊ መንገድም ፈታኝ ነው፡፡ ዐይኔ በግራና በቀኝ እያመተረ ዳገቱን ተያያዝነው፡፡ ከፍ እያሉ በሄዱ ቁጥር ቅዝቃዜው ይጨምራል፡፡ ከተራራው ጫፍ ሲደርሱ የትህነግ ቡድን በብዛት የቆፈረው ምሽግ ይገኛል፡፡ በተራራው መውጫ ላይም ውጊያውን መቋቋም ሲያቅተው ያፈረሰውን መንገድ ተመልክተናል፡፡
የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ የትህነግን ታጣቂ በቀኝ በግራ፣ በፊት በኋላ ሲያጣድፈው በጭንቅ ሰዓት አንድ ጊዜ ወደኮረም መለስ፣ አንድ ጊዜ ወደ ግራ ካሱ ግርጌ ከባድ መሳሪያ እየተኮሰ የሚሆነውን አጥቶ እንደነበር በውጊያው የተሳተፉ የልዩ ኃይል አባላት ነግረውኛል፡፡ የቦታው መመቼት፣ የከባድ መሰሪያ ክምችት ከመሸነፍ ባያድነውም፡፡ ከግራ ካሱ ጫፍ ላይ ሆኜ አካባቢውን ቃኝቼ ወደ ኮረም አመራን፡፡ ቅዝቃዜው የበለጠ እየጨመረ መጣ፡፡
‹‹ ግራካሱ ልውጣ ዳገቱን አልፌ
የእናት ጡት ማለት ነው የኮረም ኮረፌ››
ወደ ተባለላት የኮረም ከተማ እየገሰገስን ነው፡፡ አካባቢው ደጋማ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ገብስ እንደሚበቅልበትም ሰምቻለሁ፡፡ ኮረም በወሎ ክፍለ ሀገር በዋግ አውራጃ ትተዳደር ነበር፡፡ በዘመነ ትህነግ ከወሎ ክፍለ ሀገር ተነጥላ እንደ ራያ ሁሉ ወደትግራይ የተካለች ናት፡፡ ኮረም ስትነሳ የባሕላዊ መጠጥ ኮረፌ ትዝ ይላል፡፡ ኮረምን የረገጠ ሁሉ ኮረፌውን መቅመስ ይሻል፡፡ ፍቅር የሆኑት የኮረም ሰዎች አንጄት በሚያላውስ ሀገርኛ አነጋገራቸው ሲያቀማጥሉ ከተማዋን ልቀቁኝ አያስብልም፡፡ በከተማዋ ምዕራባዊ ንፍቅ ወደ ሚገኜው ኮረፌ ሰፈር አቀናን፡፡ የሕዝቡ ደስታ ልክ አልነበረውም፡፡
‹‹ጊዜ ደጉ ቀን ወጥቶ ኮረምም ልትቀረፅ ነው›› ነበር ያሉን፡፡ የኮረም ነዋሪዎች ምን ያክል ታፍነው እንደቆዩ ሁኔታቸው ያሳብቃል፡፡
ወደ ሚናፈቀው ኮረፌ ቤት ጎራ አልን፡፡ ጨዋታው ደርቷል፡፡ ‹‹አምጪ ጨምሪ›› እየተባለ ሳቅና ደስታው ደርቷል፡፡ ከመቀመጫው ጠበብ ብሎ ወደላይ ሰፋ ባለ መጠጫ ኮረፌ ይጠጣል፡፡ ደስታ አለ፡፡ ፍቅር አለ፡፡
በዚያ ቤት ውስጥ ብዙ ቀልቤን የሳቡኝ ነገሮች ነበሩ፡፡ እንደ ኮረፌ መጠጫው ዋንጫ ግን የሆነ አልነበረም፡፡ መጠየቅ ፈለኩ፡፡ ሳዬው ካስገረመኝ በላይ ስሙን ስሰማ የበለጠ ገረመኝ፡፡ ‹‹ምኒልክ›› ይሉታል፡፡ ስያሜው እንዴት እንደመጣ ጠየኳቸው፡፡ ታላቁ ንጉሥ እምዬ ምኒልክ ከኃያሌ ሠራዊታቸው ጋር ለዘመቻ ወደ አድዋ እየተጓዙ ሳለ በኮረም አቅራቢያ ደረሱ፡፡ የወፍላ ባላባቶችና ሕዝቡ በደስታ ወጥቶ ተቀበላቸው፡፡ እሳቸውን የተቀበሉበት ሥፍራም ‹‹ስንደዶ በር›› ይባላል፡፡ ትህነግ አካባቢውን ወደ ትግራይ ስታካልለው ‹‹በሪ ስንደዶ›› እንዲባል አድርጋ እንደነበርም ሰምቻለሁ፡፡
በዚያ ስፍራ የአካባቢው ደግ ሕዝብ ምኒልክን ወተትና ኮረፌ ይዞ ነበር የተቀባላቸው፡፡ ለምኒልክም ዛሬ በሚጠጣበት ዋንጫ እንዲጠጡ ሰቷቸው፤ ጠጡበትም፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ምኒልክ እየተባለ ተጠራ ይላሉ፡፡
ምኒልክ ወደዚያ ሥፍራ ከመድረሳቸው በፊት ከኮረም አጠገብ ከጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ጋር አብራ ስለምትኖር የማርያም ታቦት ዝና ይሰሙ ነበር፡፡ በዚያ ሥፍራ ሲደርሱም ስለዝነዋ በደንብ ሰሙ፡፡ በጉዳዩም በጣም ተገረሙ፡፡ ሠራዊታቸውን አንቀሳቅሰው አልፈው ወደ አድዋ ሲጓዙም ‹‹አንቺ እመቤቴ ማርያም ድል እንዳደርግ እርጂኝ ስመለስ እደብርሻለሁ›› ብለው ተስለው ሄዱ፡፡ ስለታቸው ሰምሮ ድል አገኙ፣ ሀገራቸውን እና ሕዝባቸውንም አኮሩ፡፡ በገቡት ቃልና በተሳሉት ስለት መሰረት ወደ ዋና መቀመጫቸው ሲመለሱ ቤተክርስያኗን ደበሯት፡፡ ‹‹ኃያሊቱ ማርያም›› ሲሉም ስም አወጡላት፡፡ ዛሬም ኃያሊቱ ማርያም ትባለላች፡፡ በትግርኛ ‹‹ኃያሎ›› ብለው ስሟን ቀይረውታል፡፡ አብዛኛው ግን ኃያሊቱ ማርያም ብለው ነው የሚያውቋት፡፡ ይህች ቤተክርስቲያን በግራ ካሱ አድርገው ሲሄዱ ከከተማዋ መግቢያ አካባቢ በስተ ግራ በኩል ትገኛች፡፡ ‹‹ኮረም ኃያሎ ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን›› አሁን ላይ ያለው ሙሉ ስሟ ነው፡፡
የኮረፌ መጠጫው የምኒልክ አንበሳና የእምዬ ምስል የነበረበት እንደነበርም ነግረውኛል፡፡ ድሮ የነበረውን ያክል ትልቅ ባይሆንም አሁን ድረስ ምኒልክ የሚባለው የኮረፌ መጠጫ አለ፡፡ የኮረፌ መጠጫውም እርሱ ነው፡፡ ባሕላቸውን እንዳያስተዋውቁ ጫና ሲደርስባቸው የነበሩት የኮረም ነዋሪዎች ምኒልክ የሚለውን መጠጫ ግን አልቀየሩትም፡፡ ዘመን አሻግረው አቆይተውታል፡፡
ኮረፌ ለመጠጣት የገባ ሁሉ ትካዜ አይገባውም፡፡ ሳቅና ጨዋታው ደማቅ ነው፡፡ ሰው ከሰው ጋር እንዲገናኝ ያደርገናልም ነው የሚሉት፡፡ ኮረፌ ሲጠጣ ኃይል ይሰጠናል፣ ድካም ይለቀናል፣ ለሰውነት ተስማሚ ነውም ነው የሚሉት፡፡ ለዛም ነው ወደው የሚጠጡት፡፡ ሀገሩ ገብስ አምራች ስለሆነ ኮረፌ ለመጥመቅ የተመቸ ስለመሆኑም ነግረውኛል፡፡ ኮረምን በኮረፌ እንድትታወቅ ያደረጋት በአካባቢው የሚመረተው የገብስ ሰብል ነው ብለውኛል፡፡ ኮረፌ የኮረም መታወቂያ የባሕል መጠጥ ሆኗልም፡፡ የኮረም እናቶች ኮረፌውን አዘገጃጀታቸው ውብ ስለሆነ ተናፋቂ እንደሆነም ሰምቻለሁ፡፡
ጨዋታው መልካም ነው፡፡ ቤቱ ደማቅ ነው፡፡ መገባበዝ፣ ጓደኛ ሲመጣ ተነስቶ ማስቀመጥ፣ መጨዋወት፣ ለቀጣይ ስራ በጋራ መመካከር፣ በጋራ ሆኖ ወደቤት መመለስ አለ፡፡ ኮረፌ ለጋራ ሕይወት አይነተኛው መገናኛቸው ነው፡፡ እኛም በኮረም ኮረፌ ቤት ጨዋታ ደምቀን፣ ከፍቅራቸው ተካፍለን፡፡ በኮረም ከተማ እንዳለሁ የከያኙ ግጥሞች ትዝ አሉኝ፡፡
‹‹ ብሉልኝ ጠጡልኝ ለሄደ ቤታቸው
እኒህ ወሎዬዎች አይ ልግስናቸው፡፡
ሀሳቡ ቢለቀኝ መንፈሴ ቢታደስ
የሸግዬን ሀገር አስሼው ልመለስ፡፡
ግራ ካሱ ልውጣ ዳገቱን አልፌ
የእናት ጡት ማለት ነው የኮረም ኮረፌ
ፍልቅልቅ አምደ ወርቅ ተስማሚ ለገላ
እያደር ያፋፋል የሰቆጣ ጠላ፡››
አሁን ፍቅር ተመልሷል፡፡ ጨዋታው ነግሷል፡፡ ኮረሞች ደስታ ላይ ናቸው፡፡
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleአገርን ለመበታተን አቅደው በመከላከያ ሠራዊት ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ያደረጉ ዋነኛ የጁንታው አመራሮች በቁጥጥር ስር ዋሉ።
Next articleበኩር ጋዜጣ ጥር 03/2013 ዓ/ም ዕትም