“ለኢትዮጵያዊያን የሚበጀው አብሮ መኖር፣ መተሳሰብ እና አንዱ ለሌላው ጥላ መሆን እንጂ ማሳደድ አይደለም” ፕሮፌሰር አቻምየለህ ደበላ

270
“ለኢትዮጵያዊያን የሚበጀው አብሮ መኖር፣ መተሳሰብ እና አንዱ ለሌላው ጥላ መሆን እንጂ ማሳደድ አይደለም” ፕሮፌሰር አቻምየለህ ደበላ
ባሕር ዳር፡ ጥር 02/2013 ዓ.ም (አብመድ) በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የተፈጠረው የፀጥታ ችግር ብዙዎችን ለሞት ዳርጓል፤ ከ105 ሽህ በላይ ዜጎችን ከቀያቻው አፈናቅሏል፡፡ ሀብት ንብረት እንዲወድምም አድርጓል፡፡ ተፈናቃዮች ሕዝብ እና መንግሥት ባመቻቸላቸው ጊዜያዊ መጠለያ፣ በዘመድ ቤት እና በተለያዩ ቦታዎች ተበታትነው ይገኛሉ።
ደጉ የሀገራችን ገበሬ ሞፈርና ቀንበር አስማምቶ ከማረስ ውጭ እንዲህ ዓይነት ቀን ይመጣል ብሎ በህልሙም አስቦት አያውቅም፡፡ ከሞቀ ቤታቸው ተፈናቅለው በመጠለያ የሚገኙ ዜጎችን ስቃይ እና እንግልት በቦታው ተገኝቶ ማየትም ልብን ይሰብራል፡፡ ሕዝቡ እንደ ሌላው ኢትዮጵያዊ አዛኝ፣ እንግዳ ተቀባይ፣ በሥራው ታታሪ፣ አብሮ መኖርን የሚያውቅበት እና ሀገር ወዳድ ነው፤ አሁን እደረሰበት ያለው ግድያ እና መፈናቀል በፍጹም አይገባውም ነበር፡፡
ለተፈናቃዮች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊን ድጋፍ እያደረጉላቸው ቢሆንም ለሁሉም አለመድረሱን አብመድ በቦታው ተገኝቶ አረጋግጧል፡፡
ፕሮፌሰር አቻምየለህ ደበላ በአርቲስት እና አክቲቪስት ታማኝ በየነ መሪነት የተሰበሰበውን ድጋፍ ይዘው በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የሚገኙ ተፈናቃዮችን ተመልክተዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ የዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት ያሰባሰበውን ድጋፍ ይዘው ከመጡት የልኡካን አባላት አንዱ ናቸው፡፡ ፕሮፌሰሩ “ከሞቀ ቤት ወጥቶ ወንዝ ዳር እንደመውደቅ እጅግ አሳሳቢ ነገር አይኖርም” ሲሉ ሁኔታውን ገልጸውታል፡፡ መንግሥትም የህፃናት፣ የሽማግሌዎች፣ የነፍሰጡር እናቶች፣ የአካል ጉዳተኞች እና ሰርተው መለወጥ የሚችሉ ወጣቶች ጉዳይ ሊያሳስበው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በተለይም ያሉበትን አስቸጋሪ ቦታ ግምት ውስጥ በማስገባት ወደ ቀያቸው የሚመለሱበትን መንገድ በአጭር ጊዜ ማመቻቸት ይገባል ብለዋል፡፡ ከራሱ ቀለብ በማትርፍ ለገበያ ሲያቀርብ የነበረ አርሶ አደር በመጠለያ ውስጥ መውደቁ ሰብአዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስም እያስከተለ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
የደረሰው ሞት፣ መፈናቀል እና የሀብት መውደም እጅግ አሳሳቢ የኑሮ ደረጃ ላይ እንዲወድቁ ማድረጉንም ፕሮፌሰር አቻምየለህ ደበላ ገልጸዋል፡፡ ሞትና መፈናቀሉ በተደጋጋሚ ሲደርስ መንግሥት በወቅቱ ተመጣጣኝ ምፍትሔ ሊሰጠው ይገባል ነበርም ብለዋል፡፡
“ሰፊ ሀገር፣ ሀብት እና ማንነት ያለን ኢትዮጵያዊያን የሚፈታተኑ ቡድኖች የሚለኩሱትን እሳት በማጥፋት የነበረውን የጋራ እሴት ማስጠበቅ ይገባል” ነው ያሉት፡፡ ፕሮፌሰር አቻምየለህ ዜጎች ተወልደው ባደጉት ቀየ እንዲህ አይነት አስነዋሪ ድርጊትም ሊፈጽም እንደማይገባም ተናግረዋል፡፡
የንጹኀንን ሞትና መፈናቀል ከምንጩ ለማድርቅ የመንግሥት ቁርጠኛ አቋም እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡
ለኢትዮጵያዊያን የሚበጀው አንዱ ለሌላው ጥላ መሆን፣ አብሮ መኖርና መተሳሰብ እንደሆነም ፕሮፌሰር አቻምየለህ ደበላ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

Previous articleየዳግማዊ አፄ ምኒልክ መታሰቢያ ሙዚየምና የባሕል ማዕከል
Next articleበጃንሜዳ ከ5 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ነዳያን የማዕድ ማጋራት መርሐ-ግብር ተካሄደ፡፡