“ምድር ተጨነቀች፣ ተናወጠች፣ በደሥታ ዘለለች”

500
“ምድር ተጨነቀች፣ ተናወጠች፣ በደሥታ ዘለለች”
ባሕር ዳር፡ ጥር 02/2013 ዓ.ም (አብመድ) ያየሁትን ሁሉ ለመንገር ፈራሁ፣ አቅም አጣሁ፣ ያን ተዓምር የሆነ ነገር የምገልፅበት ቃላት፣ የምናገርበት አንደበት፣ የሚበቃኝ ሰዓት ያለ አልመስልህ አለኝ። ከመገረሜ ብዛት፣ ካየሁት ነገር ፍፁም ድንቅነት የተነሳ ልቤ ተላወሰች። አንደበቴ ዝምታን መረጠች፣ ያንን የመሰለ ድንቅ ዝማሬ፣ ጥበብና ምሥጋና አይቶ አለመናገር ደግሞ ንፍግነት ሆነብኝ።
ዓለም ብትዳሰስ፣ በመብራት ቢፈለግ፣ እግር እስኪነቃ ድረስ ቢሄድ ከኢትዮጵያ ውጪ እንደዚህ አይነት ነገር ፈፅሞ ሊኖር አይችልም። ያ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዉያን ብቻ የተሰጠ ነው። መልካም ልቦች መልካም ነገርን ያስባሉ፣ መልካም ዓይኖች መልካሙን ነገር ያያሉ፣ መልካም እጆች መልካም ነገር ይሰራሉ፣ መልካም ጀሮዎች መልካም ነገር ይሰማሉ፣ መልካም እግሮች ወደ መልካም ነገር ይገሰግሳሉ፣ የታደለ አንደበት ስለ መልካም ይናገራል፣ የታደለ ሰው በመልካም ነገር ይኖራል፣ ለመልካም ነገርም ይተጋል።
“መልካም ሰው ከመልካም ልቡ መዝገብ መልካም ነገር ይናገራል፣ ክፉ ሰው ከክፉ ልቡ መዝገብ ክፉ ነገር ይናገራል” እንደተባለ ከመልካም ልባቸው መልካም ነገር ሲነገሩ ሰማሁ፣ በጥሞና አዳመጥኩ፣ ሲደረግ አየሁ፣ መልካም ነገር ባይኖርኝም በፈቃዱ መልካም ነገር ገበየሁ። ቅድስቲቷ ከተማ በደሥታ ዘለለች፤ ምድር ተናወጠች፣ ከደሥታ ብዛት የተነሳ የምትሆነውን አጣች፣ ወደላይ ከፍ ያለች መሰለች። ካህናት ዘመሩ፣ ምዕምናን እልል አሉ። የሆነው ሁሉ ከምድር አይመስልም። ቅድስቲቷን ከተማ ብርሃን መላት። ከመሬት የጧፍ መብራት፣ ከሰማይ ከዋክብት አደመቋት። በምድር ሰማይን አየሁ። ደሥታ ናጣት፣ ምሥጋና ዋጣት።
የኢትዮጵያውያን እመነት፣ የኢትዮጵያውያን ብርታት፣ የኢትዮጵያውያን ፅናት፣ የኢትዮጵያውያን አንድነት አስደነቀኝ። ቅጥር ግቢዉ በሰው ተመላ፣ ዝማሬው ደመቀ ክርስቶስ በቤተልሔም ሲወለድ ሰውና መላዕክት እንደከበቡ ሁሉ ቤተ ማርያምም በደሥታ ተመላች። ተራራዎች አበሩ፣ ካህናት ዘመሩ፣ ፀህናው ተወዘወዘ፣ ፅናንን ተፀነፀነ፣ የፅህናው ጭስ ለፈጣሪው ምሥጋና ለማቅረብ ወደሰማይ ወጣ። ዝማሬው ደመቀ፣ ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ሊቃውንት በቤተ ማርያም በምድር የሆነ ነገር ግን ምድራዊ የማይመስል ምሥጋና አቀረቡ። ከበሮው ተመታ፣ ወረቡ ተወረበ ምድር ተገረመች፣፣ ሰማይ ተደነቀች፣ አምሳለ ኢየሩሣሌም ደብረ ሮሐ ቅዱስ ላል ይበላ ጠበበች፣ መመላለሻዎች በሰው ተያዙ፣ ከማሜ ጋራ ውስጥ ከቤተ ማርያም ደጅ የሚሆነውም ታምር ለማየት የማይጓጓ አልነበረም።
የማሜ ጋራ በሰው ተጨነቀ። ጥሩንባው ተነፋ፤ እልልታዉ ደመቀ፣ ምሥጋናው ግሩም ሆነ። ቅድስቲቷ ሥፍራ ነጭ በለበሱ፣ ለምልጃና ለፅድቅ በሚገሰግሱ፣ ሳያቋርጡ በሚያወድሱ ተመላች። አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀዩ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ተውለበለበ። ለኢትዮጵያ ሰሠም፣ አንድነትና ፍቅር ተለመነ። “ኢትዮጵያ ሰላምሽ ይብዛ ተጠለይ በእግዚአብሔር ታዛ” የሚለው ዝማሬ ደመቀ። ምን አይነት ፅናት ነው ስለሀገር እየፀለዩ፣ ስለሠላም እየተማፀኑ ቆሞ ማንጋት፣ ሳያርፉ መበርታት።
ከተማዋ ከደሥታ ብዛት ተጨነቀች። የጠነከሩት ብቻ ሳይሆን የደከሙትም ተነሱ፤ ወደዚያች ቅድስት ሥፍራ በእግር የሄዱት ሁሉ ከድካማቸው አላረፉም። የበለጠ በርትተው ለምሥጋና ቆሙ እንጂ። ጨለማው በብርሃን ተመላ። በማዕልት የጀመረው ምስጋና በሌሊቱ ሳይቋረጥ አደረ። እስከ ረፋድም ቀጠለ። “ኢትዮጵያ ታበጽህ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር” እንዳለ ከዘረጋች ሳታጥፍ፣ ከቆመች ሳታርፍ፣ ወደ አምላኳ ስትማፀን የኖረችና የምትኖር ሀገር ናት። ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ዘረጋች። ከሰማይም የማይሻር ፅኑ ቃል ኪዳን ተቀበለች። “አቤቱ ኢትዮጵያን አስባት፣ ሰላም ስጣት፣ ጠላቶቿን ፈጥነህ አስገዛላት፣ ልጆቿን ባርክላት፣ ዳሯን እሳት መሃሏን ገነት አድርግላት” የሚለው የቄሱ ልመና ጭንቀት ይበትናል። ይደረጋልና ያፅናናል።
በዓለም ላይ በጥበብ ወደ ሰማይ የመጠቁ ወደ ምድር የጠለቁ፣ በጥበብ የረቀቁ አሉ። ከሁሉም ጥበብ ከሁሉም ሊቃውንት ግን የኢትዮጵያውያን ያይላል። እፁብም ነው። ከኢትዮጵያውያን የሚበልጥ ጥበብ የለም። የሚበልጥ ብቻም ሳይሆን በምን እንደሰሩት የሚያውቅ የየትም ሀገር ጥበበኛ የለም። “እስከ ሞት ድረስ የታመንክ ሁን! የሕይወትን አክሊል እሰጥሃለሁ” እንዳለ በዚያች ቅዱስ ምድር የተገኙ ሁሉ እስከ ሞት ታምነው፣ እስከ ሞት አምነው፣ የሕይወትን አክሊል ለመቀበል የተዘጋጁ ይመስላሉ።
ለምሥጋና የተጉ ናቸውና። “በተወደደ ሰዓት ሰማውህ በመዳንም ቀን ረዳውህ የተወደደ ሰዓት አሁን ነው የመዳንም ቀን ዛሬ ነው” እንዳለ ያን መልካም ነገር ለማየትና ለመስማት ጊዜው አሁን ነው። በተወደደው ሰዓትም አየሁት። በገድለ ላል ይበላ መጽሐፍ መግለጫ በሚለው የመጀመሪያው ርዕሰ ጉዳይ ላይ “ዓይናችን ሳይደክም፣ ልባችን ሳይደነዝዝ፣ ወደ ታላቂቱ የቅዱሳን ከተማ፣ ግዑዝ አለት በፈጣሪው ትዕዛዝ ለፍጡር ወደ ተገዛበት ደብረ ሮሃ ላስታ በመምጣት ቅድስቲቷን ከተማ የኢየሩሳሌም ሰማያዊት ምሣሌ ታንፃ የቃል ኪዳንና የምሕረት፣ የበረከት፣ የምሥጋና፣ የምልጃ ዝናም የሚወርድባትን የቤዛ ኩሉ ዓለም በረከት በእርሷ ብቻ የሚታይባት ሰማያዊያን እና ምድራዊውን በኢየሩሳሌም የዘመሩትን ዝማሬ በቅዱስ ላል ይበላ የሚመለከቱበትን ትልቅ አዝመራ ገነትን በፅድቅ ታዩ ዘንድ ኑ” ይላል።
አዎ ያቺ ምድር ሳትታይ የምትቀር መሆን የለባትም ኑ። ሊቃውንት ኢትዮጵያን የሰው ዘር መፀነሻ ማሕፀን፣ የሥልጣኔ መነሻ ማዕከል፣ ሀገረ እግዚአብሔር፣ የእውነተኞች ምድር፣ የነፃነት ባለቤት፣ የግዮን ምንጭ፣ የታሪክ መዝገብ፣ የዓለም ምስጥራዊ ንባብ ፣ የቅርስ መደብር፣ የውርስ መዘክር፣ የባሕል እምብርት፣ የቋንቋና የፊደል እትብት ይሏታል። በጥንታዊ ታሪክ የታወቀች፣ በስልጣኔ የደመቀች፣ በአኩሪ ገድል የረቀቀች ናት ኢትዮጵያ። ኢትዮጵያ በዜማ የምትቀደስ በቅኔ የምትወደስ፣ ምልጃዋ ከሰማየ ሰማያት የሚደርስ ሕያዊት አገር ናት። ያለ እረፍት ሠላምና አንድነት የሚለምኑ ሕዝቦች ባሉበት ምድር ስጋት አይገባም፣ በዘረጉት እጃቸው የተቀበሉት ቃል ኪዳን ኢትዮጵያውያን ዘላለም እንድትፀና ያደርጋታልና።
ማንም ክፉ ቢሆን፣ ማንም ስለኢትዮጵያ መጥፎ ቢያስብ፣ ሊወጋትና ሊያጠፋትም ቢመኝ አይቻለውም፣ ለምን ቢሉ ጠላቶቿ በዘመን ረቂቅነት፣ በጦር መሣሪያ ብዛትና ዘመናዊነት የማይችሉት ረቂቅ ምስጢር አላቸውና ኢትዮጵያውያን። ዓለም ሁሉ በኢትዮጵያ ሁለት ጊዜ ይሸነፋል፣ በመልካም ሲመኛት በፍቅር፣ በክፉ ሲመኘት ደግሞ በጦር ይሸነፋል። ኢትዮጵያን የሚያሸንፋት የለም። የማይሸነፈውን አትተውምና፣ በቅድስቲቷ ከተማ በደብረ ሮሐ ቅዱስ ላል ይበላ የታየው ሁሉ ምድራዊ የሚመስል፣ ግን ያልሆነ፣ አመሥጋኞቹ ሰዎች የሆኑ ግን የማይመስሉ፣ በዓይን የሚያዩት በህልም የሚያልሙት የሚስል። ስፍራው ሲደምቅ፣ በደሥታ ሲጨነቅ እንደቤተልሔም ሁሉ መላዕክት ከሰማይ ወርደው በላል ይበላ የሚዘምሩ ይመስላሉ።
ሊቃውንቱና ምዕምናኑ በአራቱ ማዕዘን ፈፅሞ የማይወሰን፣ በአንዲት ምክር በአንዲት ፈቃድ፣ ዓለምን ካለመኖር ወደመኖር በሥልጣኑ የፈጠረ፣ በማይመረመር ልቡና ምድርን የፈጠራት፣ ዙፋኑ የእሳት ሰረገላው የሚያስፈራ፣ የባሕር ማዕበልን እንድትናወጥ የሚያድርጋት፣ አገዛዙ ለልጅ ልጅ የማያልቅ፣ ከነገድ እስከ ነገድ የማይፈፀም፣ ጥንተ ዘመኑ የማይቆጠር፣ የአኗኗሩ ስፋት የማይወሰን፣ ይገለጥ ዘንድ ሰውን በአርኣያው የፈጠረው፣ ሰውን ያድን ዘንድ በቤተልሔም የተወለደውን ያለ እንቅልፍ ሲያመሠግኑት አደሩ። ያለ ትዕግሥት መራብ፣ መጠማት፣ መራቆት፣ መቸገርና ቃልን መፈፀም አይቻልም እንዳለ በዚያች ሌሊት ያየኋቸው ሁሉ በትዕግሥት ቃላቸውን ለመፈፀም፣ ልመናቸውን ለማስመር፣ ሀገራቸውን ለማስባረክ ሲተጉ አደሩ። ያን ያየ ፈጣሪም እንደሚሰማቸውና የምኅረት ሀገሩና ሀገራቸውን ሠላም ያደርግላቸዋል። የለመኑትንም ይሰጣቸዋል።
“ውስጡ አረንጓዴ ባሕር ቅዱስ ላል ይበላ የላስታው ደብር” እያሉ ያመሠግኑታል። በዚያች ምድር የተቀደሰችውን ሌሊት ለማክበር በአራቱም ማዕዘን ኢትዮጵያውያን ተሰባስበዋል። በዚያች ምድር ሰውነት እንጂ ዘረኝነት፣ አንድነት እንጂ ብቸኝነት፣ መልካምነት እንጂ ክፋት የለም። በአንድነት ፈጣሪያቸውን ይለምናሉ። የደከመውን የበረታው እየታቀፈ፣ እግሩን እያጠበ፣ እያጎረሰ፣ እያለበሰ፣ መቆሚያውን እያቀበለና የሚያርፍበትን ቦታ እየለቀቀ መልካም ነገር ያደርጋል። ኢትዮጵያ ማለት በዚያች ሌሊት ያየኋት ናት። ኢትዮጵያዊነት ማለትም በዚያ ያየሁት ፍቅርና ክብር ነው። አንድነት ያሳምረናል። ፍቅር ያምርብናል። እኛ የዓለም መቅኛ ሕዝቦች ነን። ዓለም በእጅጉ ትፈልገናለች። ከእኛ ውጭ መኖር አይቻላትምና።
በድብረ ሮሃ ቅዱስ ላል ይበላ የልደት በዓል አከባበርን ያየ ሁሉ መልካም ነገር አይቷል። እግሩም መሄድ እስኪያቅታት ድረስ ወደዚያች ምድር መሄዷን አታቆምም። ጆሮውም ከዚያ የተቀደሰ ነገር ውጪ መስማትን አትመኝም። ፈጣሪ ኢትዮጵያውያንን አብዝቶ ይወዳቸዋል። ሁሉንም ነገር ሰጥቷቸዋልና። ኢትዮጵያ ቅድስት፣ ኢትዮጵያ ቀደምት፣ ኢትዮጵያ ልዕልት፣ ኢትዮጵያ ቀዳሚ፣ ኢትዮጵያ ሩቅ አላሚ ናት። የቤተ ማርያም ዝማሬ፣ የቤዛ ኩሉ ውዳሴ፣ የቅኔው አዘራረፍ፣ የምዕመናን ፀሎትና ታዛዥነት አስደነቀኝ። አንቺስ ከተመረጡት የሁሉ ከፍ ብለሽ የተመረጥሽ፣ ከተለዩት የተለየሽ፣ ከከበሩት የከበርሽ፣ በታምር ተፈጥረሽ ለተአምር የተቀመጥሽ ሀገር ነሽ ኢትዮጵያ። ከፍ ያደረግሽን ትወጂዋለሽና ዘላለም ከፍ በይ።
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ ከፍተኛ ወታደራዊ ኒሻን ተሸለሙ፡፡
Next articleበ20ኛው ታላቁ ሩጫ ጽጌ ገ/ሰላማ በሴቶች አቤ ጋሻሁን በወንዶች አሸነፉ፡፡