
ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ ከፍተኛ ወታደራዊ ኒሻን ተሸለሙ፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 01/2013 ዓ.ም (አብመድ) የኢፌዴሪ መከላከያ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ፣ ከጂቡቲ መከላከያ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀነራል ዘከሪያ ሼህ ኢብራሂም የሀገሪቱ የመጨረሻ ከፍተኛ ወታደራዊ ኒሻን ተበርክቶላቸዋል።
በኒሻን ማልበስ ሥነ ሥርዓቱ የተገኙት የሰላም ማስከበር ማዕከል ኃላፊ ሌተናል ጀነራል ደስታ አብቼ እንደተናገሩት ጀነራል ብርሃኑ ከጂቡቲ መንግሥት የተበረከተላቸው ኒሻን በሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ተፈቅዶ የተሰጣቸውና የመጨረሻ ከፍተኛ ደረጃ ኒሻን ነው።
ጀነራል ብርሃኑ በወታደራዊ የአመራር ክህሎታቸው ባሳዩት ድንቅ የመሪነት ብቃት በሀገሪቱ አጋጥሞ የነበረው አደጋ እንዲቀለበስ በማድረግና ሕግ የማስከበሩን ተግባር የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት በአኩሪ ጀግንነት እንዲፈፅም የመሪነት ሚናቸውን በመወጣት ኢትዮጵያና የአካባቢው ሀገራት ከተጋረጠባቸው ከፍተኛ አደጋ በማዳናቸው የተሸለሙ መሆኑንም ገልፀዋል።
በኒሻን ማልበስ ሥነ ሥርዓቱም የጂቡቲ መከላከያ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀነራል ዘከሪያ ሼህ ኢብራሂም፣ የጀነራል ብርሃኑ ጁላን የመሪነት ብቃት አድንቀው፣ ጉዳቱን መከላከል ባይቻል ኖሮ ኢትዮጵያን በመበተን ብቻ ሳይቆም የአካባቢው ሀገራትን የሚበትን አደገኛ ሁኔታ ያጋጥም ነበር ማለታቸውን ጠቁመዋል።
ከአደጋው ሁላችንም እንድንድን ጀነራል ብርሃኑ ጁላ በተወጡት ጠንካራ አመራር ኮርተናል በማለትም ሽልማቱን ማበርከታቸውን የሰላም ማስከበር ኃላፊው ገልፀዋል።
ጀነራል ዘከሪያ ሼህ ኢብራሂም ጂቡቲና ኢትዮጵያ ያላቸው ታሪካዊ ወዳጅነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በሥነ ሥርዓቱ ወቅት አረጋግጠዋል።
ሽልማቱ የተበረከተላቸው የኢፌዴሪ መከላከያ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ፣ የሀገሪቱን ከፍተኛ የመጨረሻ ኒሻን ላበረከተላቸው የጂቡቲ ሕዝብና መንግስት በኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊትና በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ምስጋና ማቅረባቸውን የሰላም ማስከበር ኃላፊው ሌተናል ጀነራል ደስታ ተናግረዋል።
ጀነራሉ በሽልማቱ ታላቅ ኩራትና ክብር እንደተሰማቸው ጠቁመዋል፡፡
የሁለቱ ሀገሮች የሕዝብ ለሕዝብ ታሪካዊ ግንኙነትና ሀገራዊ ወዳጅነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።