ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን የግድቡ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

562
ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን የግድቡ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 01/2013 ዓ.ም (አብመድ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነትና የሚዲያ ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኀይሉ አብርሀም ከአብመድ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
እንደ አቶ ኃይሉ ገለጻ ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በተከፈተ የባንክ አካውንት የተረጋገጠ ከ790 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል፡፡ ይህም ገቢ ከ2012 ዓ.ም ከተሰበሰበው ገቢ ጋር ሲነጻጸር ብልጫ አለው ብለዋል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የመጀመሪያ ደረጃ የውኃ ሙሌቱ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለህዳሴ ግድቡ ግንባታ የሚያደርጉት ድጋፍም አጠናክረው ቀጥለዋል ብለዋል አቶ ኃይሉ፡፡ በተለይ በዓረብ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የግድቡ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠበት መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ ድጋፋቸው አልተለየንም ነው ያሉት አቶ ኃይሉ፡፡
ግድቡን የምንገነባው ድህነታችንን ለማሸነፍ ነው፤ ለዚህም የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በተባበረ ክንድ ፍጻሜ ላይ ማድረስ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ያሳለፍነው ወቅት ሀገራችን በርካታ ችግሮችን ያስተናገደችበት ወቅት ቢሆንም ለግድቡ የሚደረገው ድጋፍ አልተቋረጠም ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የቴክኒካልና የብረታ ብረት ሥራዎች በሚፈለገው መንገድ እየተከናወነ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ኃይሉ የሁለት ተርባይኖች የሙከራ ሥራ ሰኔ ላይ ለማስጀመር ታስቦ እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ግድቡ እንዲጠናቀቅ ሁሉም አካል የሚያደርገውን ድጋፍም አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል የገንዘብ ድጋፍ ለመሰብሰብም ሁነቶችን ለማዘጋጀት መታሰቡንም አቶ ሀይሉ ጠቅሰዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“በመተከል በዜጎች ላይ ለተፈፀመው ጭፍጨፋ የጉሙዝና የሌሎች ብሄረሰቦች የሥራ ኃላፊዎች እጅ አለበት” የድባጤ ወረዳ ነዋሪዎች
Next articleከ 50 በላይ ተሳፋሪዎችን የያዘ የመንገደኞች አውሮፕላን ከኢንዶኔዥያ መዲና ጃካርታ ከተነሳ በኋላ ብዙም ሳይቆይ መሰወሩ ተገለጸ ፡፡