
“በመተከል በዜጎች ላይ ለተፈፀመው ጭፍጨፋ የጉሙዝና የሌሎች ብሄረሰቦች የሥራ ኃላፊዎች እጅ አለበት” የድባጤ ወረዳ ነዋሪዎች
ባሕር ዳር፡ ጥር 01/2013 ዓ.ም (አብመድ) በመተከል ዞን በዜጎች ላይ ለተፈፀመው ጭፍጨፋና የንብረት ውድመት የጉሙዝና የሌሎች ብሄረሰቦች የሥራ ኃላፊዎች እጅ እንዳለበት የድባጤ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ።
በፌዴራል መንግስት ተቋቁሞ የመተከል ዞን የጸጥታና ሕግ ማስከበር ሥራ የተረከበው ኮማንድ ፖስት በዞኑ የተለያዩ ቀበሌዎች መሽጎ በነበረው ሽፍታ ላይ እርምጃውን አጠናክሮ ቀጥሏል።
ኮማንድ ፖስቱ ከመኖሪያ አካባቢዎቻቸው የተፈናቀሉ ወገኖችንም ተመልሶ ማቋቋምና ዘላቂ ሰላም ማግኘት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከኅብረተሰቡ ጋር ውይይት በማድረግ ላይ ይገኛል።
የኮማንድ ፖስቱን የጸጥታና ሕግ ማስከበር ሥራ የሚመሩት ሌተናል ጀነራል አስራት ዴኔሮ እና የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ጌታሁን አብዲሳ ከድባጤ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች እንዳሉት፤ በወረዳው ብሎም በዞኑ ለተፈጸመው ዘርን መሰረተ ያደረገ ጥቃትና ውድመት ከጉሙዝም ሆነ ከሌሎች ማኅበረሰቦች የተወከሉ የሥራ ኃላፊዎች ተጠያቂ ናቸው። በዚህ ወንጀል ተሳታፊ የሆኑ ሁሉ በሕግ እንዲጠየቁ ነዋሪዎቹ ጥያቄ አቅርበዋል።
የዚህ ሁሉ እልቂትና ጭፍጨፋ መሪና አቀናባሪ የትህነግ ቡድን ያቋቋመው የጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) ነው የሚሉት ተሳታፊዎቹ፤ ከጉሙዝ ወጣቶችን በማታለል ለጥፋት እየመለመለ መሆኑንም ገልጸዋል።
የጉህዴንን ውሳኔ አንቀበልም ያሉ የጉሙዝ ማኅበረሰብ አባላትም እንግልት ከማድረስ አልፎ ግድያ እንዲፈፀምባቸው እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢሳቅ አብዱልቃድር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚኖር ማንኛውም ማኅበረሰብ በሰላምና በነፃነት የመኖር መብት አለው ብለዋል።
የኮማንድ ፖስቱን የጸጥታና ሕግ ማስከበር ሥራውን የሚመሩት ሌተናል ጀነራል አስራት ዴኔሮ በዞኑ አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ኮማንድ ፖስቱ በሽፍታዎች ላይ ጠንካራ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ገልጸዋል።
እርምጃ መውሰድ ብቸኛ አማራጭ ባለመሆኑ የጉሙዝ አባቶች በተሳሳተ መረጃ ወይም በፍርሃት ጫካ የገቡ ዜጎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በርካታ ታጣቂዎችም በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን እየሰጡ መሆኑንም አመልክተዋል።
ኮማንድ ፖስቱ “በዞኑ አስተማማኝ ሰላም ሳያሰፍንና ወንጀለኞችን ለሕግ ሳያቀርብ የትም አይሄድም” ያሉት ሌተናል ጀነራል አስራት፤ ከቀበሌ እስከ ወረዳ ያሉ የሥራ ኃላፊዎች በሕዝብ የተመረጡ ይሆናሉም ብለዋል።
የወንጀል ተሳታፊ የነበሩ ሰዎች በኃላፊነት እንዳይካተቱ ከኅብረተሰቡ ጋር ሆነን የማጥራት ሥራ እናከናውናለን ሲሉም ሌተናል ጀነራል አስራት መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ