
ጥንታዊቷ አንኮበር ታሪኳን የምታስተዋውቅበት ማዕከል ተገነባላት፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 01/2013 ዓ.ም (አብመድ) ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በአንኮበር ወረዳ አስተዳደር በጀት የቱሪዝም ማዕከል ተገንብቷል፡፡ ማዕከሉ የምኒልክ መታሰቢያ ሙዚየምና ባሕል ማዕከል የተሰኘ ሲሆን ነገ ጥር 2/2013 ዓ.ም የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች ጨምሮ ከፍተኛ የክልልና የዞን መሪዎች በተገኙበት እንደሚመረቅ የአንኮበር ወረዳ ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ፈለቀ ምህረት ነግረውናል፡፡
የሙዚየሙ መገንባት በ18ተኛው ክፍለ ዘመን የነበሩ የነገሥታቱ ብርቅዬ እቃዎች ወደ ሙዚየሙ ሲገቡ ለጎብኚዎችና ተመራማሪዎች ክፍት የሚሆኑበት እድል ይፈጠራልም ተብሏል፡፡
በ333ዓ.ም እንደተመሰረተች የሚነገርላት አንኮበር የበርካታ ነገሥታት መናገሻ ሆና አገልግላለች፡፡ አንኮበር በተፈጥሮ ከታደለችው የብዝኃ ህይወት ሃብትና ማራኪ ቦታ አቀማመጥ ባሻገር የጥንታዊ አብያተ ቤተክርስቲያናት መገኛ በመሆኗ በርካታ ቅርሳቅርሶችም አሏት፡፡
በየቤተክርስቲያናቱ ተበታትነው የሚገኙ ጥንታዊ ቅርሶች አዲስ በተገነባው የምኒልክ መታሰቢያ ሙዚየምና ባሕል ማዕከል ገቢ ሆነው ለጎብኝወች ክፍት ይሆናሉ ተብሏል፡፡
በአካባቢው ከሚገኙ 97 ጥንታዊ አቢያተ ቤተክርስቲናት ውስጥ ያሉ ልዩ ልዩ ቅርሶች ተሰባስበው ወደ ማዕከሉ ይገባሉ፡፡
125 ዓመት ያሰቆጠረ የአጼ ምኒልክ ካባና 2 ጎራዴ፣ ጥንታዊ የብራና መጻሕፍትና ሌሎችም ወደ ማዕከሉ ገብተው እንዲጎበኙ ይደረጋል፡፡ ይህ ማዕከል መገንባቱ አንኮበርን ከቱሪዝም ሃብት ተጠቃሚ እንደሚያደርጋትም ተመልክቷል፡፡
ዘጋቢ፡- ሸምስያ በሪሁን
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ